Ethiopian news and information update

ደቂቀ ገሞራ

በዚህች በእኛ ምድር ፣ በዚህች በእኛ ሰማይ በኢትዮጵያ ከብዙ ከዋክብት ልቀው የሚታዩ ነበሩ፡፡ ዛሬም አሉ፡፡ እነዚህ ከዋክብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ እውቅና ካገኙት ከእነ ቪክተር ሁጎ፣ ከማክሲም ጎርኪ፣ ከሔሚንግዌ፣ ከአቼቤ፣ ከሶይንካ፣ ከማህፉዝ ናጉዪብ፣ ከንጉጊ፣ ከቶልስቶይ፣ ከዲከንስ እንዲሁም ከመሳሰሉት ጨቋኝ ሥርዐቶች በሚያደርሱት ግፍ የጉስቁሉን ህዝብ መከራ በስነ-ጽሑፋቸው ፍንትው አድርገው እንዳሳዩት ሁሉ የኛዎቹ የኢትዮጵያ ከዋክብትም በብዕራቸው ባይልቅ የሚስተካከል በረከት አበርክተዋል፡፡ የጨቋኝ ሥርዐቶችን የሚገለማ ጠረን፣ የሚያሰጸይፍ ገጽታ፣ የሚዘገንን ጭካኔ፣ ጥርስ የሚያስነክስ አረመኔነት፣ በአጠቃላይ እኩይ ባህርያትን በብዕራቸው ተዋግተው የተዋጊውን ህዝብ መንፈስ ለትግል አነሳስተዋል፡፡ ዛሬም ድረስ እያነሳሱ ነው፡፡ ግን የነዚህ የኢትዮጵያ ከዋክብት ስም በበርካታ የብዙሀን መገናኛዎች አይወጋም፡፡ በአንዳንዶቹ ያውም የህዝብ ነን በሚሉ የብዙሀን መገናኛዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚደርስባቸው ተጽዕኖ የነዚህ ከዋክብቶች ስምና ሥራ በጨረፍታ እንኳ ሲወሳ ለማድመጥም ይሁን ለማንበብ አልታደልንም፡፡ ለአብተነት ለመጥቀስ የሀማ ቱማ ድንቅዬ ግጥሞች፣ አጫጭር ልብ ወለዶች፣ ምጸታዊ የፖለቲካ ትችቶቹ ህዝባዊ ነን በሚሉ ድርጅቶች ድረ-ገጾች፣ ቴሌ ቪዥኖች፣ ሬድዮኖች፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች እንዲሁም በስነ-ጽሑፍ ምሽቶች አለመቅረባቸው በእህህ ብቻ ታፍኖ እስከመቼ እንደሚቀጠል ግልጽ ሆኖ አይታይም፡፡ ለዴሞክራሲ እንታገላለን ከተባለ የሀማን ሥራ ማቅረብ ሊታለፍ አይገባውምና በዓይነ ህሊናቸው አንጎላቸውን እንዲያነቡት በዚሁ አጋጣሚ እንዘክራለን፡፡

ዛሬ ገሞራው አረፈ ሲባል ስሙን ሲጠሩት ዓይኖቻችንን ከድነን ታዘብናቸው፡፡ አንደዜም ልሳናቸውን ከፍተው ማይምር ደብተራው ፀገየ ወይንን ወያኔዎች የት አደረሱት ሳይሉ ኢሕአፓ የጸገየ ወይንና የሌሎች ኢሕአፓዎች በወያኔ መገደላቸውን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ ሲያነቡ ለሚሰማው መልስ አልባ እንቆቅልሽ እንደሚሆንበት ጥርጥር የለውም፡፡ ደብተራውና ገሞራው ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ኩልል፣ ንጥር ፣ ጥርት ያሉ ውሀ ናቸው፡፡ ሁለቱም በግዕዝ ፣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ እጅግ የመጠቀ ችሎታ ያላቸው በመሆናቸው ሊቀ ሊቃውንት ሊባሉ ይገባቸዋል፡፡ ሁለቱም በዜማ፣ በቅኔ ጥልቅ፣ ምጡቅና ባህር የሆነ እውቀት እንደነበራቸው ከሥራዎቻቸውና በቅርብ ከሚያውቋቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በባህርያቸውም ቢሆን የሰውን ልጅ በማህበረ-ሰቡ ውስጥ ባለው ቦታ፣ በሀብቱ፣ በትምህርቱ፣ በእድሜው፣ በዘሩ ሳይሆን የሚያከብሩት በሰው ልጀነቱ ብቻ ነበር፡፡ የመኮፈስ፣ የአጉራ ዘለልነት፣ የአውቄ በቃሁነትና ባህርያት የሁለቱም ጠላቶች ናቸው፡፡ ታናናሾቻቸውን እንደ እኩዮቻቸው በማየት ሰርስሮ የሚገባ ፍቅርን የሚለግሱ ናቸው፡፡ እንኳን ለሰው ልጅ ለእንስሳትም ልባዊ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ገሞራውና ደብተራው ቅኔዎቻቸው በረከትን በህዝብ መፈቀርንና መደነቅን እንዳጎናጸፏቸው ሁሉ መርገምንም አሳርፈውባቸዋል፡፡ በአጼው ዘመን ለእስር ተዳርገው ስቃይ መከራ ተቀብለዋል፡፡ ወገናቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በጭቆና እየተገረፈ፣ ገበሬው በእንባ ዓይኖቹ እየሟሙ፣ ሠርቶ አደሩ አንጀቱ እየደማ ባለበት፣ ወታደሩ የአገሩ የወገኑ ዘብ መቆም ሲገባው ለጥቂቶች በመቆም ህዝብን አሳር በሚያሳይበት ሁኔታ ተድላና ደስታን እርግፍ አድርገው ሳይሸራርፉ ሙሉ ህይወታቸውን ለጉስቁሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰጡ፡፡ የቅኔ ዘረፋ፣ የመወድስ ድርደራ ከነዚህ ከዋክብት በላይ ለማን ይደረጋል፡፡

ዕድለኞች አሉ፣

ወለም ዘለም ያላሉ፣

የወገናቸውን ሰቆቃ መከራ ሊከሉ፣

ሎጋ ህይወታቸውን፣

ምትክ አልባ ነፍሳቸውን፣

ከአንጀት ለሚወዱት፣

ተድላ ደስታውን ሊያጎናጽፉት፣

ገና በማለዳ አሀዱ ሲል፣

አሏህ ወአክበር ሲባል፣

የቅኔያት ዘር ዘሩ፣

እኔን፣ አንተን፣ እሷን ኮረኮሩ፣

ተክላቸው ፀገየ-አበበ፣

ጥቁር ጥላን በአይነኬዎቹ ላይ ደበበ፣

ፀሐይ ለአፈር-ገፊው፣

ለተራበው ለተጠማው፣

አንጀቱ የታጠፈውን ለመታደግ፣

ለከሲታው ለአፈርማው፣ ብርሀኗን ፈንጠቅ ስታደርግ፣

ተጋረደ በምራጭ ወታደሩ በደርግ፡፡

የፀገየው ፍሬ ፍራፍሬ፣

የተዘራው ጥሬ ጥራጥሬ፣

አቤት ሲያምር እርሻ ሞልቶ፣ ከአገር እስከ ዳር ሰርፍቶ፣

ቀነየ ቀነየ ሳብ እረገብ፣

ሲዘምሩ ሲያዜሙ ዋ! እያሉ፣

ተምቾች አበቦችን ቀነደሉ፣

የአበቡ የፀገዩትን ሁሉ፣

ምን ቢንደላቀቁ ምን ቢበለጽጉ፣

ምን ቢወሻክቱ ምን ቢመላገዱ፣

የፀየው ገሞራ ከቶ አይቀርላቸው፣

አቃጥሎ፣ አንድዶ፣ አንፍሮ ይፍጃቸው፡፡

የፀገየ ደብተራው ናስተማስለኪ፣ የኃይሉ ገሞራው በረከተ መርገም የተጻፉት የአጼውን ዘመን ግፍ ለማሳየትና ለመርገም ለመኮነን ነበር፡፡ ድምጸታቸው ዛሬም ድረስ ያስተጋባል፡፡ ዛሬም አገራችን ኢትዮጵያን ናስተማስለኪ ስንል አንድ ከመቶ የማይሞሉት ወያኔዎችንና አጉራ ዘለል አጫፋሪዎቻቸውን ሳይሆን ከመቶው ዘጠና ዘጠኝ የሚሆነውን ጉስቁል፣ ምዝብር፣ በረሀብ፣ በበሽታ፣ በፊደል ጥማት የሚሰቃየውን ማለት መሆኑ ደምቆ ይሰማል፡፡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ በጣሊያን ወረራ ዘመን በስደት በነበሩበት ወቅት የቋጠሯቸው ስንኞችም እንዲሁ ለዛሬው የጠባቦቹ የጭቆናና የግፍ ዘመን ያስተጋባሉ፡፡

ረሀቤ ጥሜ እርዛቴ ሦስቱ፣

ይደበድቡኛል በአንድ እየዶለቱ፡፡

በዚህ ሃያ አንደኛ በሚባለው ዘመን በዓለም የአንደኝነት ደረጃን አትንኩብኝ በሚለው በአምባ ገነኑና በአረመኔው ወያኔ በፍትህ ርትዕ ላይ የተመሰረተ የሀብት ክፍፍል ባለመኖሩ ጥቂት ህዳጣኖች በሚሊዮን ቁንጣን እቅብ እቅብ በመተንፈስ ሲሰቃዩ፤ ህልቆ መሳፍርቱ ህዝብ በጠኔና በችጋር በነፍስ ውጪ በነፍስ ግቢ ህይወት ይማቅቃል፡፡ ገሞራው በበረከተ መርገም ባነሳቸው ጭብጦች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የሰው ልጅ በእድገቱ፣ በሥልጣኔው የፈለሰፋቸው ቁሶችና የፈለሰማቸው ይትበሀሎች ለሰው ልጅ ጠቀሜታነት መዋላቸው ቀርቶ ለሰው ልጅ ጥፋትና ውድመት መዋላቸውንና ይህን እኩይ ድርጊት አስፈጻሚና ፈጻሚዎችን ኮነነ፡፡ እረገመ፡፡ ውጉዝ ከመ አርዮስ አላቸው፡፡ እንደ አርዮስ ይለዩ ይረገሙ፡፡ ዝነኛው፣ አንጋፋው ዘፋኝ ዓለማየሁ እሸቴ ያቀነቀነው ፀረ- ኮሎኒያሊዝም የሆነው ያ ጥቁር ግሥላ የተሰኘው ግጥም የደብተራው የጸገየ ወይን ነው፡፡ ስንኞቹ የጸገየ ወይንን የመጠቀ ቅኔ ዘራፊነት ይመሰክራሉ፡፡

በረከተ መርገም ዛሬም ድምጹ በቅኔው ማህሌት በተዘረፈበት ዘመን ሳይቀነበብ የዛሬው ግፈኛ፣ ዘራፊ፣ ዘረኛና ደም አፍሳሽ የሆነው ወያኔንም ከነግፉ ከነግሳግሱ ነፋሪት ያንፍርህ ይለዋል፡፡ ነገም በህዝብ ስም በዴሞክራሲ ስም ሥልጣን ኮርቻ ላይ ፊጥ ለማለት አንዴ ለአሜሪካ፣ ሌላ ጊዜ ለአውሮጳ ብዙ ጊዜ ለሸአቢያ የሚያጎነብሱትን፣ የነጭ ነጫጭባን ጫማ የሚልሱትንም ነጎድጓደ መብረቅ ይባርቅባችሁ ይላቸዋል፡፡ በምዕራቡ ዓለም የፖለቲካውን ሞተር የሚዘውረው በህዝቡ ተመረጠ የሚባለው መንግስት መሆኑ ቀርቶ የነጋዲያን ኃይል መሆኑን በመረዳት ይመስላል ጥቂት የማይባሉ ምህንድስና፣ ምጣኔ-ሀብት፣ ህክምና የተማሩ ሊሂቃን በምዕራብ አገራትና በአገር ውስጥ ህጋዊ ተብዬ ድርጅት መሪዎችን ገሞራው ከመጠምጠም መማር ይቅደም፤ አሻፈረኝ ካሉም የዳሎል ገሞራ አቃጥሎ ይፍጃችሁ ይላቸዋል፡፡ በጋዜጠኝነት ስም የቀጣሪያቸው አገልጋይ በመሆን ሲጠሯቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት የሚሉ ምርኮኛ ለሆዳቸው ለከርሳቸው ያደሩትን እንደ ጋሪ ፈረስ የሚጋለቡትን ጋዜጠኞች እግዚአብሔር መልሶ በየእናታቸው ማህጸን ይቆልፍባችሁ ይላቸዋል ገሞራው፡፡ ገበሬውን ደም ዕምባ የሚያስነቡትን፣ የህጻናት ጉልበትን የሚያስበዘብዙትን፣ ልጃገረድ እህቶቻችንን ለአረቦች እየፈነገሉ የሚሸጡትን፣ ለሠራተኞች አግባብ ያለው ደሞዝ የማይከፍሉትን አውሎ ነፋስ ጠራርጎ እንጦርጦስ ያውርዳችሁ ያላቸዋል   ማይዕምር ገሞራው፡፡ የአማራ ገበሬን በማንነቱ ብቻ ከእርሻውና ከቀየው የሚያፈናቅሉትንና ህጻናቱን የሚያርዱትን፣ እናትና ልጆችን የሚደፍሩትን፣ ለድንበር ዘለል የባዕድ የእርሻ ኩባንያዎች የጋምቤላን፣ የኦሮሞን፣ የመዠንግርን፣ የአማራን ገበሬዎች ያፈናቀሉትንና በጥይት የረሸኑት ወያኔዎችን ንፍር ውሀ ያንፍራችሁ ፡፡ መሸሺያ መሸሸጊያ አይኑራችሁ ዘንዶ ይዋጣችሁ ይላቸዋል ገሞራው፡፡ ወያኔዎች ትምህርትን በአፍጢሙ ደፍተውትና ተረግጠውት እንደገና መልሰው ትምህርትን እናጠራለን እያሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች ላይ በመዘበታቸው ገሞራው የዱር አንበሶች ቦጭቀው ቦጫጭቀው አክተው ይፍጇቸው ያላል፡፡ ህክምናና መድሀኒትን እንደ ሰማይ አርቀውበት በተለያዩ ደዌዎች ህዝቡን ለአልጋ ቁራኛ የዳረጉ፣ እናቶችን ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሞታቸውን የሚያጣድፉትን፣ ህጻናትን በበሽታ የሚቀጩትን፣ አረጋውያንን በበሽታ አማቀው የሚገድሉትን፣ ወጣቶችን በተለያዩ ሱሶች የሚያስለክፉትንና በበሽታ እድሜያቸውን የሚቀጩት ወያኔዎችን የአንበጣ መንጋ በመርዝ ይፍጃቸው፡፡ ሙጥጥ ያርጋቸው ብሏል ገሞራው፡፡ ለከርሳቸው ለሆዳቸው ሲሉ ለአረመኔው ወያኔ ያደሩ አድር ባዮችን የቆማችሁበት ምድር ተከፍቶ ይዋጣችሁ ብሎ ገሞራው መረቃችሁ፡፡ በሀይማኖች አባትነት በሙስሊሙም በክርስቲያኑም በወያኔ የተሾማችሁ በሀይማኖት ስም የምታመነዝሩ ጳጳሳት ቀሳውት ወሼሆች በቁማችሁ የንፍር ውሀ አንፍሮ ቀቅሎ ሙክክ ያድርጋችሁ እያለ ገሞራው እረገማችሁ፡፡ ለአረመኔው መለስ ያለቀሳችሁ ዘፋኞች፣ ያነባችሁ ከያኒዎች፣ ደረት የደቃችሁ የማስታወቂያ ጡሩምባ ነፊዎች፣ ለሆዳችሁ ብላችሁ ዓይናችሁን የጨመቃችሁ ዶክተር መምህራን ወሐኪሞች ገሞራው የሎስ ስንጥቅጥቅ ያርጋችሁ ብሎ አከበራችሁ፡፡ የሀሰት የእድገት ቁጥር የምታወሩ አለቃ ወምንዝር ወያኔዎች አንዳች አዙሪት አዙሮ አዙሮ ገሞራው ፍግም ድፍት ያድርጋችሁ ብሎ አሞካሻችሁ፡፡ በነጻ ጋዜጣ ወመጽሔት ስም የምታደናግሩ የወያኔ ሪፖርተሮች፣ ፎርቹኖች ወሌሎችም ከየግድግዳው ለትሞ አጋጭቶ ይድፋችሁ በሉልኝ ብሏል ገሞራው፡፡

ፀገየ ወይንና ገሞራው ድምጻቸው አንድ ነው፡፡ ሁሌም ዋ! ዋ! ዋ! እያለ ይጮኻል፡፡ እነዚህ ሁለት ከዋክብት የበርካታ ከዋክብት ወኪሎች ፋና ወጊዎች ናቸው፡፡ ዘራቸው ፀግይቶ፣ አብቦ፣ አፍርቶ መጎምራቱ አይቀሬ ነው፡፡ የበሰለው ፍሬም ለህዝቡና ለህዝቡ ልጆች አብነት ሲሆን ለህዝብ ጠላቶች ግን ገሞራ ነው ፡፡ ያቃጥላል፡፡ ያንጨረጭራል፡፡

Comments on: "ኮከብ እም ከዋክብት ይሄይስ ክብሩ" (1)

  1. […] ደቂቀ ገሞራ፡  ገሞራው በበረከተ መርገም ባነሳቸው ጭብጦች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ የሰው ልጅ በእድገቱ፣ በሥልጣኔው የፈለሰፋቸው ቁሶችና የፈለሰማቸው ይትበሀሎች ለሰው ልጅ ጠቀሜታነት መዋላቸው ቀርቶ ለሰው ልጅ ጥፋትና ውድመት መዋላቸውንና ይህን እኩይ ድርጊት አስፈጻሚና ፈጻሚዎችን ኮነነ፡፡ እረገመ፡፡ ውጉዝ ከመ አርዮስ አላቸው፡፡ እንደ አርዮስ ይለዩ ይረገሙ፡፡ ዝነኛው፣ አንጋፋውና ህዝባዊ  ዘፋኙ ዓለማየሁ እሸቴ ያቀነቀነው ፀረ- ኮሎኒያሊዝም የሆነው ያ ጥቁር ግሥላ የተሰኘው ግጥም የደብተራው የጸገየ ወይን ነው፡፡ ስንኞቹ የጸገየ ወይንን የመጠቀ ቅኔ ዘራፊነት ይመሰክራሉ፡፡ በረከተ መርገም ዛሬም ድምጹ በቅኔው ማህሌት በተዘረፈበት ዘመን ሳይቀነበብ የዛሬው ግፈኛ፣ ዘራፊ፣ ዘረኛና ደም አፍሳሽ የሆነው ወያኔንም ከነግፉ ከነግሳግሱ ነፋሪት ያንፍርህ ይለዋል፡፡  ሙሉውን ሐተታ ያንብቡ … […]

Leave a comment