Ethiopian news and information update

(Read in pdf)

ሐተታ ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ

 

የኢትዮጵያና የሕዝቧ መሰረታዊ ችግሮች ከስርዓት ወደ ስርዓት እየተለጉ ቀጥለዋል። ቀጣይ በመሆናቸውም ሕዝብ መብትንና ብልጽግናን ተነፍጎ በጭቆና ተረግጦ መገዛት ዕጣ ክፍሉ ሆኖ ቀጥሏል። ገዢዎች በየፊናቸው የችግሩን ይዘትና ክፉነት ከመካድ ባሻገር ለዚሁም ተጠያቂው ሌላ ነው በማለት የብዝበዛ ስርዓታቸውን መቀጠል ልምዳቸው ነው። በአፄው ጊዚ የነበሩ መሰረታዊ ችግሮች ዛሬም ሳይቀረፉና ሳይወገዱ–ያውም ተባብሰው- በመቀጠላቸው ኢትዮጵያ ለሕዝቦቿ የመከራና ግፍ መሬት ሆና ትገኛለች።

ችግሮቹ ግን ሰው ሰራሽ፤ የአገዛዞቹ የተዛባ ፖለቲካ ውጤት ነበሩ፣ናቸውም። ብዙሀኑን ይመለከት የነበረውና ያሰቃየው የመሬት ለአራሹ ጥያቂ በቅድሚያ የተከሰተው በአርሶ አደሩ ላይ ገባርነትና ጪሰኝነት ስለተጫነ ነበር። መሬት ለአራሹ ብለው የተሰለፉት ተማሪዎች መፈክሩን ከገዋ ላይ፤ እንደምትሀት የፈጠሩት አልነበረም። ገበሬው ምርቱንም መሬቱንም ስለተቀማና ይህ በደልም በመብት ጥሰት በመታጀቡ የአርሶ አደሩ ጥያቄ–የመሪት ለአራሹ መፈክር– ዋና ሆኖ ተገኘ። ተማሪዎችም ይህን መፈክር አንግበው በመሰለፍ ከነበረው ስርዓት ጋር የሚቆራረጡበትና አልፎም ከጥገና ለውጥ አማራጭ ወደ ስር ነቀል ለውጥ አቅዋም የሚሸጋገሩበት ሆነ። ችግሩ በአጼው ጊዜ መፍትሄ ቀርቶ በቂ ማስታገሻ ሊያገኝ ባለመቻሉ ለተራማጆች ና ለአርሶ አደሩም ትግል መሰረትና ነዳጅ ሰጪ ሆኖ ቀጥሎ የየካቲት አብዮትን ካስነሱት አንዱ ጥያቄ ሊሆን ቻለ። ይህንን መሰረታዊ ጥያቄ ደርጉ አስገራሚ ሊሆን በቻለው ውረሰው፤እፈሰው ግደለው ገምድል ፖለቲካው መሪት የመንግስት ብሎ ራሱንም መንግስት አድርጎ ገበሬውን የአገዛዙ ጪሰኛ አድርጎ ችግሩን አባባሰው። አርሶ አደሩም ምርቱን ኮታ በሚባለው ውሳኔ መሰረት ተዘረፈ። ወያኔ ስልጣን ሲይዝ ደግሞ የደርጉን እርምጃ ቀጥሎና ራሱ ዋና መሬት ቀሚ ሆኖ እነሆ ችግሩ እስከዛሬም ብሶና ተባብሶ ይገኛል። የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት መብት በቅድሚያና በሙሉ በማክበር ብቻ ነው። የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የተነሱ ገዢና ከበርቴ ክፍሎች የአርሶ አደሩ ሞግዚት መስለው የሚያቀርቡት ሌላ መፍትሄ ሁሉ ውድቅ ነው።

የኢትዮጵያ ሌላ ዋናው ችግር የዲሞክራሲ መጥፋት ነው። የአጼው የንጉስ ስርዓት መብትን ለንጉሱ የሰጠና መሰረታዊ መብቶችን ያገደ ነበር። የደርግ ወታደራዊ ፋሺስታዊ አገዛዝ ደግሞ ጸረ ሕዝብ ስለነበር ጸረ ዲሞክራሲነቱን ራሱም ሊክድ የሚችል አልነበረም። የወያኔ አገዛዝ ደግሞ በአንድ ብሄረሰብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ዘረኛ ጸረ ሕዝብ ጸረ ኢዮጵያ–ስለዚህም ደግሞ ጸረ ዲሞክራሲ–አረመኔ አገዛዝ ነው። በ ሶስቱም አገዛዞች ሕዝብ መብት አልባ ተደርጓል። በሕዝብ አብዮት የአጼው አገዛዝ ሲያከትም ሁሉን አቀፍ የሆነና ዲሞክራሲን መሰረት ያደረገ ጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግስት ተመስርቶ የዲሞክራሲ ሽግግር ይደረግ የተባለውን መኮንኖቹ አሻፈረን ብለው የራሳቸውን ወታደራዊ አስተዳደር መስርተው ወደ አፈናው ሒዱ። የእኩልነትን ጥያቄ በዲሞክራሲያው መንገድ መፍትሒ እንስጥ ሲባሉም አይሆንም ብለው ችግሮችን በጦርነት ሊፈቱ ተነሱ–አባባሱት። ሰራተኛውን ማህበር አልባ አደረጉ፤ የሲቪል ተቋማትን በሞላ አፍነውና አፍርሰው የራሳቸውን መሰረቱ። በስመ ሶሻሊዝም የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት ሰፈነ። መድብለ ፓርቲ ተወገዘናም ድርጅቶች ላይ አስከፊ ጭፍጨፋና ሽብር ተካሄደ። ዲሞክራሲ ዕጣዋ በይ ደህና ሁኚ ወግጂ ሆኖ ተገኘ። ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሳይሆኑ ስርዓቶቹ የፈጠሩትና ያባብሱትም የብሂረሰብ ችግር–በተለይም በኤርትራ– የሚያዋጣ መፍትሒ ሊሰጠው ሲገባ በመኮንኖቹ ጭፍን እብሪትና ግድያ ለግንባሮቹ በሚያመች ሁኔታ ተባባሰ።የንግግር ነጻነት፤ የፕሪስ ነጻነት፤የመደራጀት ነጻነት፤ የስራ ማቆም አድማ መብት፤ ወዘተ ሁሉ ተከለከሉ። ዲሞክራሲ በጠፋበት ደግሞ ዕድገትም ሆነ ሰላም አይገኝምና ኢትዮጵያ የጦርነት አውድማ ሆነች። የጭቆናው ስርዓት ቀጠለ። ወያኔም በዋና መልኩ በዚሁ ነው የቀጠለበት። የጎረናው ላይ ደግሞ የራሱን ጸረ ኢትዮጵያ፤ዘረኛና ገንጣይ አቅዋም አክሎበታል። እኩልነትን አመጣሁ፤መብትን አበሰርኩ ቢልም ለራሱ ክልል ግንጠላ የሚያመቸውንና በኢትዮጵያ አንገት ላይ እንደ ዲሞክሊስ ጎራዴ ጥፋት የሚቃጣውን አንቀጽ 39 ደነገግ እንጂ ሁኔታው ያው የሕዝብ ጭቆናና የትግራይ የበላይነት፤ አድልዎና በደል፤ ጸረ ሕዝብነትን ያቀፈ አገዛዝ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ከድጡ ወደ ማጡ ከገባንም 23 ዓመታት እየመረሩን አልፈዋል።

የሀገር ሉዓላዊነት ጥያቄም ያው ከጌታ ጌታ እየተቀየረ የሚቀጥል ተደርጓል። በአጼው ዘመን የእንግሊዙ ቢከሽፍም አሜሪካ በሀገራችን መሬት የጦር ሰፈርን አግኝታ የአገዛዙ ደጋፊና ተቆጣጣሪ በመሆን በሀገራችን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሉዓላዊነትን ተጻራ ቆይታለች። ደርግም ሲባል ሰምቶ ኢምፒሪያሊዝም ወዘተ በሚል በአሜሪካ ላይ ቢነሳም ሀገራችንን ለሩሲያ አስረክቦ ነበር። ወያኔ ደግሞ ከጫካ ጀምሮ ራሱንና ትግሉን ለባዕዳን የሸጠ በመሆኑ አሜሪካ እግር ስር ለመውደቅ ጊዜ አልፈጀበትም። አሚሪካም የወያኔና ሻዕቢያን ዓላማ ደግፋ ሀገራችን በወያኔ ለመያዟ ሆነ ለኤርትራ መገንጥል፤ከዚያም ለወያኔ በስልጣን መበርከት ከፍተኛውን አስተዋጾ አድርጋለች፤እያደረገችም ነው። በወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያ ራሷ ሕልውናዋ ለጥያቄ የገባ በመሆኑ ስንት የጀግና ደም የፈሰሰለት ለም መሬቷ ለሱዳንም ተችሯል። ለቻይና፤ለሳውዲ፤ ለህንድም ተሽጧል። ወያኔና የሀገር ሉዓላዊነት ሆድና ጀርባ ናቸው–ከመነሻ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚያምን አይደለምና። የሀገራችን ሉዓላዊንት አለመከበር ደግሞ ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ማጠናከር የሚለውን ሕልም አድርጎ አስቀርቶታል። የሀገራችን ኢኮኖሚ በወያኔና በባዕዳን ተይዟልና፤ አረብ፤ቻይና፤ህንድ ቅድሚያና የበላይነት አግኝተዋልና ብሄራዊ ኢኮኖሚውን ሊያጠናክሩ ይችሉ የነበሩት ዜጎች ከባድ ጋሪጣ ተዘርግቶባቸዋል። ኢኮኖሚያችን በአሃዝ ደረጃ አደገ ቢባልም ከብሒራዊ ዕድገትና ከሕዝብ ብልጽግና/ዕድገት አንጻር ጫጭቷል። ይህም ሌላ በየስርአቱ የቀጠለ ጉዳይ ነው። ብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚጠይቃቸው እርምጃዎች አልተወሰዱም፤ የሚወሰዱም አይደሉም። ወያኔ ደግሞ ብሄራዊ ኢትዮጵያው ሀይል አይደለምና የነሱ ብልጽግና የኢትዮጵያ ስቃይ እንጂ ጸጋ አይደለም፤መቼም ሊሆንም አይችልም።

የስርዓት አገልጋይና የአፈና ሀይል ሳይሆን የሀገርን ድንበር ጠባቂ ሰራዊት ይኑረን የተባለውም በሶስቱም አገዛዞች ሰሚ አጥቶ ጦሩና ፖሊሱ ለገዢዎች የጭቆና መሳሪያ ሆኖ ቀጥሏል።ባለፉት ሁለት ስርዓቶች የጦሩን ይዘት ዛሬ ካለውም በስፋት ይለያል። ያለፉት የገዢዎች ታዛዥ ሆኑ ብንልም እንደዛሬው የአንድ በሄረሰብን የበላይነትን የሚያንጸባርቁ ጦሮች አልነበሩም። አሁን በወያኔ ግን ጦሩ በአብላጫው በትግራይ ጀኒራሎችና መኮንኖች የተያዘ የአንድ ድርጅትና በሄረሰብ የበላይነት የሰፈነበት ነው። ህዝብን በማፈንም ሚናው ከቶም የማይናቅ መሆኑና ለዘረኛው ስርዓት ሙሉ በሙሉ የቆመ ሀይል መሆኑን እንገነዘባለን። በወያኔ ስር ያለውን የአፈና ሀይል የኢትዮጵያ ጦር ወይም ሀይል ብሎ መጥራቱ የሚያምና የሚጎረብጥ ጉዳይ ነው። በዚህ በኩል ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ የሚለው መንግስት ምርጦ ባለማቋቋሙ አገዛዞችና ህዝብ ለየቅል ሆነው ባጅተዋል። ይህን ያልተረዱ ክፍሎች አሁንም ቢሆን ወያኔ ሊያደናግር ሀገር ወዳድ ሀይል ወይም ለሀገር ተቆርቋሪ መስሎ ለመገኘት ሲውገረገር ዋና ደጋፊ ሆነው ራሳቸውን ያስገምታሉ። የወያኔን የ ህዳሴ ግድብ ቧልትና ደጋፊዎቹን ያጢኗል! የወያኔን ወረራ በሶማሊያ ይገነዘቧል! ተልዕኮው ግንባታ ወይም ሰላም ሳይሆን ሌላ ነው። ጉዳይ አስፈጻሚነቱ ለሀገር ሳይሆን ለባዕድ ነው።

ከመብት አንጻር የሲቶችና የሕጻናት መብት ይከበር የተባለውም ምላሽ መነፈግ ሳይሆን ከአገዛዝ ወደ ሌላ ስንወረወር ችግሩ እየተባባሰ ሂዶ በተለይ በወያኔ የሲቶችና የሕጻናት መብት በ አሰቃቂ ደረጃ ተረግጦ ተደፍሮ መገኘቱ ምስጢር አይደለም። ሕጻናትን መሸጥ፤ ለአቅመ ሒዋን ያልደረሱትን ለሴተኛ አዳሪነት መዳረግ፤ መድፈር፤ ወጣት ሴቶችን ለዘመናዊ ባርነት መሸጥ የወያኔ መለያዎች ናቸው። ወያኔ ሲቶችና ወጣቶች ህጻናትን የሚጎዱ ባህሎችንና ድርጊቶችን ይሁነኝ ብሎ ማስፋፋቱ ምስጢር አይደለም። በ ጤናና በትምህርት መስክም ከክልል 1 – ከወያኔ ክልል– ውጪ ያሉት የሚደርስባቸው ችግር የሚታወቅ ነው። የገዢ ክፍሎች ልጆች በውጭ ሀገርና አገልግሎታቸው በተሟሉ ትምርት ቢቶች ሲማሩ የብዙሃኑ ህዝብ ልጆች ግን የትምህርት በቂ ዕድል ተነፍገው ይገኛሉ። የትምህርት ደረጃው ዝቅ ማለትና መንኮታኮት ደግሞ ከበፊት የጀመረ ቢሆንም (በደርግ ጊዜ) በወያኔ ደግሞ ኡ ኡ የሚያሰኝ ደረጃ ላይ አለ። ተምሮ የጨረሰውም ስራ አጥነትን ከዲፕሎሙ ጋር ያገኛል። በፖለቲካው፤ በኢኮኖሚው ና በህብረተሰቡ ጉዳዮች ሁሉ የነበሩ ችግሮች መፍትሄን አጥተውና ተባብሰው አሉና አገዛዙ ለዚህ ዋና ተጠያቂና ደንቃራ በመሆኑ መወገዱ ለችግሮች መፈታት ቅድመ ሁኔታ ነው። ይህን ሀቅ በመካድ ወያኔ በራሱና ባሰለፋቸው ጋዜጠኛና ምሁር ተብዪዎች አማካይነት የሰላም ህዳሴ፤ ዕርቅ፤ ሌላ አብዮት አያሻንም ወዘተ በሚል መደረግ ያለበትን ቁርጠኛ ትግል ለማደናቀፍ ተነስተዋል። ኢአግ ለትጥቅ ትግል ሲነሳ “መላ ወይስ ዱላ” የተባለውን ዓይነት ነው። በዚሁ መልክ ዛሬ በወያኔ ላይ ሕዝባዊ አመጽ እንዳይስፋፋ ነጻ ጋዜጠኞች በሚል ሽፋን ያንን የታገለ ትውልድ የሚያወግዙና ሰላማዊ ለውጥ (ህዳሲ ይሉት ጀምረዋል) በሚል ወያኔን ሊያድኑ የተነሱ አሉ። ይህ ለአገዛዝ እያደሩ የሕዝብን ትግል የሚያደናቅፉ ከሀዲዎች ክስተት አብሮን የዘለቀ ነው ። በአጼውም ጊዜ የመፈንቅል ሙከራዎች በከሀዲዎች የተነሳ ከሽፈዋል፤ በደርግም የተለየ አልተከሰተም። ወያኔ ደግሞ ሆዳሙን መግዛትና ማሰለፍ ይችልበታል–ሰርጎ ገቦቹም ብዙ ናቸው። የከሃዲዎች መፍላት የችግራችን አካል ሆኖ ከርሞብናል፤ጎድቶናል፤ ዛሬም እየጎዳን ያለ ነው። መሰረታዊ መፍትሄ ፈላጊ ችግር።

የሀገራችን መሰረታዊ ችግሮችን ማወቅና መፍትሄያችውንም አውቆ እውን ለማድረግ መታገል ወሳኝና ተቀዳሚ ግዳጃችን ነው፤ አሊያም ሊሆን ይገባል። ችግሮቹም እንዴት ተነሱ፤ለምንስ ብቅ አሉ ብሎ ለማወቅ መነሳትም ያስፈልጋል። ለችግሮች ሁሉ ለሀገር የታገሉና የተሰዉትን ወይም ኢሕአፓን ማውገዙ ወያኔነት ነው። ለጸረ ሕዝቦች ወንጀል ማጠየቂያ የሚደረድሩ ደግሞ ከሕዝብ ጎራ ነን፤ ለችግሮች መፍትሄ ፈላጊ ነን ቢሉ የሚታመኑ አይሆኑም። የሀገራችን ዋና ዋና ችግሮች የአገዛዞቹ ጥፋቶች ናቸው። መፍትሄ ሲሹ ሲፈልጉ ዜጎች ቢሳሳቱ ችግሩን ፈጣሪ አያደርጋቸውም። ሀቀኛ ዚጎች እንጂ። ለዲሞክራሲ ያለንን ፍላጎት የሚያደናቅፉ ደንቃራዎችና ሀይሎች ማን ናቸው ብለን ስንነሳ ወይም መፍትሄ ለመፈለግ ስንጥር መንገዱን የሚዘጉብን–ወያኔዎች ሆኑ የሕዝብ ወገን መስለው ለወያኔ ያደሩ እባቦች–የትግላችን ዋና ጠላቶች ናቸው–ልክ እንደ ወያኔ። እነዚህም ዛሬም እንደ ትላንት የመሰረታዊ ችግራችን አጃቢዎች ናቸው።

መፍትሔዎቹ እምቢ ተባሉ እንጂ ግልጽ ናቸው። መሬት ለአራሹ፤ ያልተገደበ ዲምክራሲያዊ መብት ለሰፊው ጭቁን ሕዝብ፤ ሉዓላዊነት ለኢትዮጵያ፤ ብሂራዊ ኢኮኖሚን ማጠናከር፤ ገለልተኛ የውጭ ፖለቲካ፤ የሀገር አንድነት በዲሞክራሲ መሰረት፤ኢትዮጵያዊነት…ሁሉም ለወያኔ ጸር ናቸው። ሀገር አድኑ ትግል በግድ የወያኔን አገዛዝ ማክተም መወገድ ይጠይቃል። ለዚህ ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ ሆነን እንገኝ።

ጸረ ወያኒ ትግላችን ይፋፋም!

አወናባጆችና አድርባዮችን እናሳፍራቸው !

 

Leave a comment