Ethiopian news and information update

ከዓለሙ ተበጀ

“አንተ ወጣት! …” አሉኝ። የፈጠራ ሥነጽሁፍ መምህራችን ጋሼ ዘሪሁን በእውነተኛ ገጠመኛችን ላይ የተመሰረተ አንድ አጭር ልብወለድ እንድንጽፍ አዞን ነበር። ለዚሁ የቤት ሥራ የሚሆነኝ ገጠመኝ ለመቃረም ወደ ጠጅ ቤት ሄጄ ከጎኔ የነበሩት አዛውንት ናቸው እንዳ ያሉኝ። የአዲስ አበባው ካምፖዲያ ጠጅ ቤት፣ ከ6 ኪሎ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መሄጃ ላይ፣ ከነዳጅ ማደያው ፊት ለፊት። ዓመቱም 1981።

“አንተ ወጣት!…” ደገሙ። ወደ እሳቸው ዘወር አልኩ። ብርሌያቸውን አንሰተው አንድ ጊዜ አንደቅድቀው መልሰው አስቀመጡና “አንተ ወጣት!…” አሉን ለ3ኛ ጊዜ ደግመው።

”አቤት አባቴ።“ ከፈገግታ ጋር መለስኩላቸው።

”አንተ ወጣት ስልህ ተዘረጠጥኩ ብለህ እንደማይከፋህ ተስፋ አለኝ። …” በይቅርታ አስተያየት እየተመለከቱ ተናገሩ።

”በፍጹም! ምንም አልከፋኝም።“ ስላቸው ፊታቸው ይበልጥ በደስታ ፈካ። እኒህ ጥቁር የሃዘን ኮፊያ ያደረጉና ገብስማ ጺማቸው የተንዠረገገ ሽማግሌ፣ ክሳታቸው የደምግባት ውርሱን ሊያጨልመው ካልቻለው ውብ ፊታቸው ጋር ፈገግታቸው ተጨምሮ ሲስተዋሉ የደስ ደስ አላቸው። ሞቅታም ዳር ዳር ብሏቸዋል።

”አንዳንዶቹ ይከፋቸዋል! ይገርመሃል!…” በሰፊው ተነፈሱና ጠጃቸውን አንደቅድቀው በመጨረስ፣ አስተናጋጁ መጥቶ እንዲቀዳላቸው ለመጥራት ብርሌያቸውን ካግዳሚው ጋር ደጋግመው አጋጩት። አስተናጋጁ ወደ እኛ መምጣት ሲጀምር፣ ንግግራቸውን ቀጠሉ። “… ይገርመሃል! አንዳንዶቹ ይከፋቸዋል! እናት አባታቸው ያወጡላቸው ስም እንደቀረባቸው ሁሉ በእሱ ካልጠሯቸው ይከፋቸዋል! … ውሸቴን እንዳይመስልህ! ይከፋቸዋል!… “ ከእኔ መልስ ይጠብቁ ይመስል አተኩረው ያስተውሉኝ ጀመር።

”እንደት?” የጨዋታቸው ውል አልያዝህ ብሎኝ ጠየኳቸው። አስተናጋጁ ደርሶ ሲቀዳላቸው ዓይኖቻቸውን ወደዚያው ወረወሩና በብርሌው ግርግዳ እየተንኳለለ የሚወርደውን ጠጅ በፍቅር ያስተውሉ ጀመር። አስተናጋጁ ሲሄድ ነበር፣ ፊታቸውን ወደ እኔ የመለሱት። ጨዋታቸውን እንዲቀጥሉልኝ ደግሜ ጠየኳቸው:

“እንደት?”

“ጓድ በሉን ይላሉ። ጓድ በሉን ይላሉ በግድ። ጉዳይ ኖሮብን ለማስፈጸም ከቢሯቸው ሄደን … ምን ቢሮ ብቻ … መንገድም ላይ ድንገት አፋችን ሳት ብሎት … መቼም ልብ ያላዘዘው አፍ ችግር አይደል … አቶ እገሌ ካልናቸው ፊታቸውን ያጨፈጉግብናል አንዳንዶቹ ተመራጮች! እኛ ዱሮ ጓድ የምንባባለው ባለን ፍቅር፣ ሞታችንን ሞታችን፣ ደስታችንን ደስታችን አድርገን እርስ በእርስ የምንቀበል የልብ ጓደኛሞች መሆናችንን ለመግለጽ ነበር። … ታዲያ እናንተስ ልጆቻችን የምትታገሉልን እኛ እድሜያችን ወደመገባደዱ የደረስነው ባንደርስበትም እንኳ ጥጋብ ደስታ የሞላበት ህይወት ልታተርፉልን አይደል?” አሉና ንግግራቸው ገተው ትክ ብለው አዩኝ። ለጥያቄያቸው መልስ እንዲሰጣቸው የፈለጉ ይመስላል። አዎንታዬን ጭንቅላቴን በመነቅነቅ ገለጽኩላቸው። ብርሌያቸውን አንስተው ብዙ ጠጅ ተጎነጩና ከቦታው መልሰውት ቀጠሉ:

“. . . ታዲያ እኛው ያገለግሉናል ብለን በመረጥናቸው፣ በእኛው ላይ አድልዎ እየሰሩብን፣ በእኛው ላይ ፍርድ እያጓደሉብን . . . እንደው ለነገሩ . . . ጓድ ብንላቸው ህሊናችንን አይቆጠቁጠንም?. . . ” ለትንሽ ጊዜ ጸጥ አሉ። ሞቅታቸው እየጨመረ መጥቷል። የእልህ ፈገግታ ብልጭ አደረጉና ቀጠሉ። “. . . ህ! እኔ አባትህ ደግሞ የምፈራቸው አይምሰልህ!. . . ፊት ፊት እንኳ ጓድ የማልላቸው አፌን እየሳተው ነበር። አሁንማ ሲታወቀኝ ነው ይህንን ባልሆኑበት ማዕረግ መጠራት የሚፈልጉበትን ቃል ትቼ አቶ እገሌ የምላቸው እነኝህ ሌቦች!? . . . እንደዚህ ጠርቻቸው እነሱ ሲከፋቸው ሳይ ታዲያ እኔ አንጀቴ ይርሳል! አንጀቴ ቅቤ ይጠጣል! ደግሞ እንዲህ በቀላሉ የምተዋቸው አይምሰልህ! በሚቀጥለው የቀበሌያችን ስብሰባ ጉዳቸውን ነው የምዘከዝከው። ምናለ በለኝ! ከዚህ ከሚኩራሩበት ተመራጭነት አስወርጄ ሃቀኞች እንዲተኳቸው ባላደርግ እንኳ ህዝብ ፊት አጋልጣቸዋለሁ! ህ! ምን ይመጣል? መታሰር፣ ግፋ ቢል አንድ ሞት. . . ዘይገርም አሉ አባቴ። ጣሰው ይሙት አለቃቸውም!” እጃቸውን ልከው አሁንም ጠጃቸውን አንደቅድቀውለት ብርሌያቸውን አስቀመጡና “. . . ቆይ! አሁን ቴያትር ነው የማሳይህ” ብለው ከኛ ትንሽ ራቅ ብሎ ሲጫወት በመቆየት ሽልማቱን ተቀብሎ ሊሄድ የነበረውን አዝማሪ ጠሩት። አዝማሪው መጥቶ ማሲንቆውን እየቃኘ እንደቆመ ወደ እኔ ጠጋ ብለው “ያንን ከፊት ለፊታችን የአብዮት ጥበቃ ልብስ ለብሶ የተቀመጠውን ሌባ ቀስ እያልክ ተመልከተውማ” አሉኝና ግጥም ይሰጡት ጀመር።

“ያልሞተበት የለም. . .” ሽማግሌው ላዝማሪው ነገሩት። አዝማሪው ደገመ:
“ያልሞተበት የለም. . .”
“ያልቀበረ ሬሳ. . .”
“ያልቀበረ ሬሳ. . .” አሁንም ደገመ አዝማሪው።
“ጨዋታ ነው እንጂ. . .” ቀጠሉ ግጥማቸውን ሽማግሌው።
“ጨዋታ ነው እንጂ. . .” አዝማሪው ተቀበላቸው።
“ሁሉን የሚያስረሳ. . .” ሽማግሌው አሁንም ሰጡት የሚቀጥለውን ስንኝ።
“ሁሉን የሚያስረሳ. . .” አዝማሪው ስንኙን ደግሞ ሲያዜም፣ ሽማግሌው አሁንም ወደ እኔ ጠጋ ብለው:

”አየኸው አይደል! ይህን ሌባ ገና የእኔን ድምጽ ሲሰማ ዘወር ብሎ ሲገላምጠኝ?” እውነታቸውን ነበር። ብርሌያቸውን አንስተው ተጎነጩና ቀደም ሲል የተነገረውን ስንኝ እየደጋገመ ሲያዜም ለነበረው አዝማሪ:

“ከእንግዲህ ዘመቻ . . .” በማለት ሽማግሌው ግጥም መስጠታቸውን ቀጠሉ።
“ከእንግዲህ ዘመቻ . . .” ተቀበለ።
“ሊቀመንበር ይምራ . . .” ተከታዩን ሰጡት።
“ሊቀመንበር ይምራ . . .” አዝማሪው ተቀብሎ አዜመ።
“ከኋላ በመቅረት . . .” ሽማግሌውም ቀጠሉ።
“ከኋላ በመቅረት . . .” ደገመ አዝማሪው።
“ገንዘብ እንዳይበላ . . .” ተከታዩን ስንኝ ሰጡት ሽማግሌው። አሁንም ከጠጃቸው ተጎነጩና ከበፊቱ ይበልጥ ጎላ ባለ ድምጽ:

“አየኸው አይደል ይህን ሌባ ሁላ?! ሌባ ሁሉ! ፈስ ያለበት ዝላይ አይችልም እንዲሉ አንጀቱን ነው የማሳርርለት! ደግሞ እኔ አባትህ የተኮስኳት ጥይት ብቻ አትምሰልህ ወፍ የምታወርደው?. . . ለግጥምም ወደር ያለኝ እንዳይመስልህ! አንጀቱን ነው የማነድለት!” አሉኝ ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብለው። በጨዋታችን መካከል አዝማሪው የተቀበላቸውን ስንኞች ደጋግሞ እያዜመ ነበር። ፊታቸውን ወደ እሱ መለሱና ቀጠሉ ግጥም መንገራቸውን:

“የጉቦን አቅማዳ . . . አዋጁ ቀዷታል፣
”ሊቀመንበር ሰፍቶ . . . ይጠቀምባታል፣
“ቤቶች ዓይን ታመው . . . ሲደነባበሩ፣
“ባስመሳይ ተመራጭ . . . ባረቂ ተመሩ።” አዝማሪውም የየስንኞቹን ግማሽ ግማሽ በየተራ እየተቀበለ አዜመ። ሽማግሌው የመጨረሻውን ሀረግ ተናግረው ሲያበቁ በኩራት ተኮፍሰው፣ በሠፊው ተነፈሱና ብርሌያቸውን አንስተው ተጎነጩ። ዓይኖቻቸውን እየዞረ ወደሚገላምጣቸው አብዮት ጠባቂ ወርወር አደርገው አዩና ጨዋታቸውን ቀጠሉልኝ።

(ይቀጥላል)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: