Ethiopian news and information update

(Read pdf)

ሐተታ ቁጥር 3  (ግንቦት 2006 ዓ. ም.)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ የሀገሩ ባለቤት ፤ በሀብቷና በረከቷ ተጠቃሚ፤ የኅልውናዋ ጠባቂና ተንከባካቢ፤ ለምልዕነቷና አግማሷ ቀናዒ ሆኖ የኖረ ለመሆኑ፤ ማስረጃ ማምጣት አለብህ የሚባል ሕዝብ አይደለም ። ይህንን ሀቅ ፤እርሱ እራሱም ሆነ ዓለም የሚያውቀውና የሚያረጋግጠው ነው ። ሌላው ይቅርና፤ በአስራ ዘጠነኛው ምዕተ- ዓመት መገባደጃ አካባቢ አፍሪካን ለመቀራመት በበርሊን ከተማ የተስበሰበው የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ጉባዔ፤ የሌሎቹን አፍሪካ ሀገሮች በመቀራመት፤ የየግላቸው ቅኝ ገዛቶች ለማደርግ ሲሉ የቆየውን ወሰናቸውንና ዳር ደምበራቸውን እያመሰቃቀሉና እየብውዙ አፍሪካን ቢከፋፈሏትም፤ ሀገራችንን ግን አልሞክሯትም። አልደፈሯትምም። በማድጎ ደረጃም ቢሆን እንኳ ፤ የሞግዚትነት ሚና እንጫወት ብለው ለማታለል አልሞከሩም። ሞክረውም ከሆነ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በመሆኑም፤ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ለጉዲፈቻ መጠባበቂያ ሊዳርጓት የሞከሩ የውስጥ ጠላቶችና የውጭ ባላንጣዎች ሙከራቸው ስለከሸፈ የሀፍረት ሸማ ተከናንበው ቀርተዋል። የውጭ ጠላቶች በመጡበት እግራቸው ተዋርደው ሲመለሱ፤ ሀገር-በቀል የውስጥ ባንዳዎች ደግሞ ወደ ማየቅርላቸው የታሪክ እንጦሮጦስ ወርደዋል ። የታሪክ ማስረጃ ካስፈልገ፤ ሩዶልፎ ግራሲያኒን እና ሃይለ ሥላሴ ጉግሳ አረዓያን ጠቅሶ ማለፍ ይበቃል።

ያን ሁሉ ጥቃትና በደል ተቋቁማ ህልውናዋን ለመጠበቅ እየተውተረተረች የቆየችው ሀገራችን፤ ዛሬ ፤ ያ የቆየው ታሪኳና ክብሯ፤ እንዳልነበረ ሆኖ፤ ዜጎቿ በማንነት ፈለጋ እንዲተረማመሱ እየተደረጉ ናቸው። ከኢትዮጵያዊነት አግማስና ክብር ፤ ከብሄራዊ ምልዑነትና ጉራማይሌነት ይልቅ፤ ዜጎቿን ፤ ሽርፍራፊና ንዑሳን መንደርተኞች ሆነው በክልል ተገይደው- ተኮድኩደው አንዱ የሌላው ባዕድና ጠላት እንዲሆን እየተደረግ ነው ። “ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል አርበኛ ሲጠፋ ባንዳ ይነግሳል “ እንዲሉ ለመላዋ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና ልዕልና ፤ ለዜጎቿ ዕኩልነትና አንድነት፤ ለፍትኅ-ርትዕ ፤ለደሞክራሲና ዕድገት የታገሉና የተዋድቁ ዐርበኞችና ሰማዕታት በየወኅኒ ቤቶች እየተሰቃዩና እየጠፉ፤ የኢትዮጵያ አጥፊዎች ጨርሰው እንዲያጠፏት ዕድሉና ሁኔታው ተመቻችቶላቸዋል። የሃይማኖትና የጎሳ አክራሪነት፤ ዛሬ የኢትዮጵያን ኅልውና ለከፍተኛ አደጋ ከሚጥሉት አደጋዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ናቸው። ሀገሪቱንና ዜጎቿን ግን ከጥቃታቸውና ጭንቀታቸውም ሊታደጋቸው የቻለ ኢትዮጵያው ኃይል እስካሁን አላገኙም ። ስማዕታቱ ይህን ቢታዘቡ ፤ ከመካነ- መቃብራቸው ውስጥ እንደሚገለባበጥ አንጠራጠርም።

ያለመታከት ደጋግመን እንደምናሳስበው፤ ሀገራችን እንደ ሀገር፤ ዜጎቿም እንደ አንድ ሕዝብ እንዳይኖሩ የመጨረሻው በር ከተዘጋ በኋላ፤ የኢትዮጵያን ተስካር ለማውጣት ተሰብስበን እንላቀስላት ማለቱ አይጥቅምም። ይህ እንዳይሆን አስቅድመን ብልሃት ይፈልግ ብለው የተናገሩትም ቢሆን ከተጠያቂነት ነፃ ይሆናሉ ማለት አይደለም ። ይህንን ማስፈሩ ፤ ለታሪክ ማጠያቂያነትና ማመሳከሪያንነት ምናልባት ይረዳ ይሆናል ከሚል ቀቢፀ ተስፋ ሳይሆን ፤ ዕውነቱ መነገር አለበት ከሚል የማረጋገጫ ግንዛቤ ነው ። ያም ሆኖ፤ እየተጠራሞተች ያለችው ሀገራችን በምንም መንገድ ቢሆን የማደጎ ልጅ /ጉድፈቻ አትሆንም። የመጨርሻው ኢትዮጵያዊ ዐርበኛ ክንዱን እስከሚንተራስ ደረስ ሀገራችንን የመታደጉ ትግል መቅጠሉ አይቀርም ! ልብ ያለው ልብ ይበል። ልብ ካለው ወገኑ ጋርም ልብ ለልብ የግባባ ! ልብ ለልብ ከተግባቡ የልባሞች ብልሃት ጠፍቶ አይጠፋምና !

ሞግዚትም ይሁን ማደጎ አሳዳጊ ለመሆን የሚሞከረው እኮ፤ ወላጅ ያጣ ልጅና ባለቤት የሌለው ሀገር ሲኖር ነበር! በረዥም አኩሪ የታሪኳ ሂደት በሀገርችን ይህ ክስተት ስላልነበረ ኢትዮጵያ ዕጓለ ማውታ ልትሆን አልበቃችም ነበር። እስከ ግንቦት 1981 ዓም ደረስ ኢትዮጵያን የገዙት ቀደምት አምባገነኖችም ቢሆኑ፤ ለሥልጣናቸው ሲሉ ሕዝቡን አፈኑ-ጨቆኑ፤ ተቃዋሚዎቻቸውን ገደሉ- ጨፈጨፉ፤ ዜጎችን አደኅይተው -አደንቁረው ገዙ እንጅ ፤ ሀገራችንን እጓለ- ማውታ አደርገው ለማደጉ ልጅ አላዘዋወሯቱም ። ለጉዲፈቻ አልዳረጓትም ። “ ከኛ የበለጠ ኢትዮጵያ አይገኝም “የሚሉ ነበሩ ስለሚባልላቸው ፤ በሀገሪቱ ምልዕውነት ይደራደሩ ነበር ተብለው ሊታሙ የሚችሉ አልነበሩም የሚሉ ወገኖች ቁጥራቸው በጥቂቱ የሚገምት አይሆንም።

ምንም እንኳን “ከፋፍልህ ግዛ “ የሚለው የአጋዘዝ ስልት፤ የአምባገነን ሥርዓት አራማጆች ሁሉ ዓይነተኛ መመሪያቸው ስለነበረ፤ ሕዝብ እንዳያምጽባቸው ተቃዋሚዎቻቸውን እየከፋፈሉና እያዳከሙ ማጥፋታቸው የተወቀ መሆኑ ባይካድም፤ የኢትጵያን ሕዝብ በቋንቋና በሃይማኖት እየከፋፈሉ እንዳሁኑ፤ የሀሪቱን ኅልውና አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል መፈጸማቸውን ሕዝቡ አያስታውስም ። ሀገሪቱ ባለቤትና ለደኅንነቷም ተጠያቂ የሚሆን ኃይል አጥታ፤ ተከራካሪና ጠባቂም ሳይኖራት ቀርቶ ለማደጎ ልጅ አልተዳረገችም ነበር። ለውጭ ኃይሎች ጉዲፈቻ አልተወረወረችም ነበር ።

ዛሬ ግን ሁኔታው ሌላ ሆኗል። በዘር የተደራጁት ዘርኛ ቡድኖች፤ ውኅዳን በመሆናቸው፤ ዘጠና ሚሊዮን የሚሆነውን ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ “ አንቀጥቅጠው ለመግዛት “ የሞከሩት፤ በእነርሱ ችሎታና ሃይል ሳይሆን፤ ለረዥም ዘመን፤ የኢትዮጵያን መበታተን አበከርው ይመኙ በነበሩት የቅርብና የሩቅ ባላንጣዎች ሙሉ ትብብርና ደጋፍ በመስጠታቸው እንደሆነ የሚያከረክር አይደለም። ዎያኔዎቹ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ ያላቸው የመረረ ጥላቻና የመጨረሻ ደማኛነት፤ የሚረጋገጠው፤ ሕዝቡን በዘር እየከፋፍሉ ሀገሪቱ እንድትበጣጠስ መፍጭረጨራቸው ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያም አርፈው-ተርፈው ፤ የሀገሪቱን ዜጎች ፤ በኢትዮጵያዊነታቸው ኢትዮጵያዊ መንግሥት አቋቁመው ማንነታችውን የሚያከብርላቸውና የሚያስጠብቅላቸው ኃይል አሳጥተው ፤ወላጆቹን እንዳጣ ህጻን ፤ ለማደጎ እንዲዳረጉ ማድረጋቸው ነው። ያም ሆኖ፤ ዛሬ ሀገራችንን በማደጎ ሊያሳድጋት እንኳን ፈቃደኛ የሚሆን ተቆርቋሪ ወዳጅ መኖሩን እንጠራጠራል።

ዛሬ የዓለም አቀፍ ህግም ይሁን በዚህ ህግ አምኖ የሚተደደረው የዓለም ኅብረተሰብ ፤ ስለያንዳንዱ ሀገር የግዛት አንድነትም ይሁን የነጻነት ልዕልና ሲቆረቆርና ጥብቅናም ቆሜአለሁ ሲል እንሰማልንም። ለዴሞክራሲ ሥርዓት፤ ለሰው ልጅ ነጻነትና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አፈ-ቀላጢ ነኝ ብሎም ሲውሸክት እያዳመጥን ነው። ይህ ሁሉ ዝማሬና ዲስኩር ግን ለኢትዮጵያ አልበጀም። የዓለም አቀፍ ህግ የሚባለውም በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ሲሆን አልታየም። በአንጻሩ ግን ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ በድሏታል ። ጎድቷታል ። አድልዎም ፈጽሞባታል ። ሀገራችን ለመሥዋዕት ጠቦት መዳርጓ፤ በታሪክ እየተደጋገመ ተከስቷል።

ይኽን አባባላችን፤ በሁለት የታሪክ ማስረጃዎች አስደግፈን ማረገገጥ እንችላለን። ኢትዮጵያ አባል ሆና ትሳተፍበት የነበረችበት የመንግሥታት ማኅበር በ1933 ዓም ( እ.አ.አ.) የፋሽስት ኢጣልያ ጦር ፤ የማኅበሩን ህግ በመጣስ ሀገራችንን በመውረር፤ በመርዝ ጋዝና ናፓል ቦምብ ሕዝባችንን ስትጨርስ ፤ አባል መንግሥታቱ፤ የኢትዮጵያን አቤቱታ ጆሮ ዳባ ብለውት ቀርተዋል ። ሀገራችንንም ለመሥዋዕት ጠቦት አሳልፈው ሰጥተዋታል ። ይህ የበደል ድርጊት ልክ ከአምሳ ስምንት ( 58) ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ላይ እንደገና ተፈጽሞባታል። በአስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ 1991 ዓም ( እ.አ.አ.) ኢትዮጵያ ከ 1945 (እ.አ.አ.) ዓም ሲመሰረት ጀምራ አባል የሆነችበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ( የ.ተ.መ ድ. ) ኢትዮጵያ ባልተውከልችበትና ህግ ወጥ በሆነ መንገድ የሀራችንን የነጻነት ልዕልና፤ የግዛት አንድነትና የፖለቲካ ሉዋላዊነትን የሚዳፈር ውሳኔ በማስተላልፍ እንደገና ሀገራችን እጓለ ማውታ እንደትሆን ተደረገ። ይህንን ሁሉ የምንመዘግበው ፤ ለጥቃትና ለቁጭት ማገመሚያ ይሆናል ብለን ሳይሆን፤ ወይም ደግሞ እንዳይረሳ ለማሳሰብ ተብሎ ሳይሆን፤ በሀገራችን ላይ በተደጋጋሚ የተፈጽመውን ግፍ ፤ነግ -ከነግ ወዲያ በማያዳግም መልኩ ፤ የሀገራችን ጥቃትና በደል እንዳይመጣ፤ የሚያስችለንን የማንነት መተመመኛ ለማስረግጥ መቻላችንን ካሁኑ ማስብ ያለብን መሆኑን ለመጠቆም ነው ። ለዚህ ፍቱን መዳህኒት ደግሞ የተባበረ ብሄራዊ ትግል ማካሄድ ይሆናል። ጥቃት ተሰምቶት፤ ቁጭቱን ለመወጣት የማይታገል ትውልድ፤ከባርነት ቀምበር ይወጣል ተብሎ አይታሰብም።

ወያኔዎቹ ፤ ይህንን ሲሰሙ “በፈርስ ላይ ማጓጎር ነው “ ብለው ለማፌዝ እንደሚሞክሩ እንገነዝባለን። እኛ ደግሞ፤ ትንሣዔ ኢትዮጵያን ለማየት ለዕድሜያችሁ ዕድሜ ይስጠው እንላቸዋለን ! ይህንን አባባል፤ ቆጭቱን ቋጥሮ፤ ነገር ግን ጥቃቱን ለመወጣት የሚጠባበቅው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ይረደዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን የቤት ሥራ ሳንሰራ ቀርተን ወይኔና ተባባሪዎቹ አጠቁን! በደሉን ብለን የምንናገርበት ልሳን ሊኖረን የሚገባን አይመስለንም ። አንድ አዝማሪ፤ ”እነርሱ ምን ያድርጉ? ከኛ ሰው ሲታጣ ! “ ብሎ በመዘመር የብዙ አድማጮቹን የተሰበረ መንፈስ እንዳነቃቃ እንረዳለን። “ “ቤታችውን ሳይዘጉ ቀርተው በሌባ ያመካኛሉ ! “ የሚል ተረት በሕዝባችን ላይ እንዲተረትበት አንሻም ! የፉክክር ቤት የሚዘጋው ጠፍቶ ክፍት በማደሩ፤ የሌባና የዘራፊ ሲሳይ እንደሚሆን ፤ የደርግ መሪ የነበረው ግለስብ ተዋጊውን ሠራዊት ጥሎ በመሸሽ የሀገሪቱን ዳር ድምበር ከፍቶ ለወያኔ መጫዎቻ ማድረጉ ተጨባጭ ማሰረጃ ነው። በመንግሥት ሥልጣን ላይ ትኮፍሶ፤ “እስከ መጨርሻዋን ጥይት ደረስ እውጋለሁ “ ሲባል የነበረው የአደባባይ ድንፋታ ሀገሪቱን ከውርደት አላዳናትም ! የአንድን ሀገር ስትራተጂያዊ ጠላት፤ ከግል ሥልጣን ተቅናቃኞች ለይቶ አለማዎቅ፤ በአንድ ሀገር ላይ ምን ያህል ዘላቂ ጉዳት እንድሚያምጣ የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በሚግባ ያስገነዝባል።

ለአላፉት ሃያ ሦስት ዓመታት በሀገራችን የተፍጸመውንና እየተፈጸመ ለለው ብሄራዊ ወንጀልና ጥፋት መሠረታዊ ምክንያት ፤ የሀገራችን ሕዝብ ከሊኅቅ እስክ ደቂቅ በሚገባ ተረድቶት ሁኔታውን በመሠረታዊና በማያዳግም መልኩ ለመለወጥ በመታገል ላይ ይገኛል ። ለትግሉ መነሻና ዓላማ ያደረገው ፤ሀገሩን ከጥፋት ማዳን ሲሆን ፤ የቁጣው ዒላማ ያነጣጠረው ደግሞ ፤ በሀገር ውስጥ አምባገነኖችንና በውጭ ተባባሪዎቻቸው ላይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ዓላማውን ሊመታ የሚችለው ግን በተባበረና በተቀነባበረ ኃይል ሲመራ ብቻ መሆኑ አያከራክርም።

የኃይል ሚዛኑን ወደ ትግሉ እንዲያመዝን ከተፈለገ ደግሞ እስካሁን ሲደርግ ከነበረው አመለካከትና አያያዝ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ ፤ጥራት ባለው ሁኔታ የተለየ ለውጥ ሲያደርግ ብቻ ነው። የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ሲባል፤ በአሁኑ ወቅት፤ በሀገራችን የሚታየውን የኃይል አሰላለፍ፤ አፈረጃጀት፤ ተቃርኖም ይሁን ዝምድና በየደረጃው እየተነተኑ መረዳት ማለት ነው። ወዳጅንና ባላንጣን በሚገባ አውቆ መታገል ፤ካልታሰበ ውድቅት ያድናል። ከዚህ ግንዛቤ ለመድረስ ደግሞ፤ ሁለንተናዊ አመለካከትና ካድማስ ባሻገር እየተመለከቱ ከየግል ድርጅት በላይ ማስብን ይጠይቃል።

ተወደደም ተጠላ ፤ የሀገራችን የፖለቲካ ምልከዐ-ምድር በጠቅላላው፤በሁለት ጎራ መከፍሉን መረዳት ተገቢ ይሆናል። በአንድ በኩል በዘር የተደራጀውና ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠሏ ቅርቶ ዜጎቿ በየዘራቸው ተከፋፍለው እንደሆኑት ይሁኑ ብሎ የሚያቀነቅነው ክፍል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፤ በኅብረ- ብሄር ተደራጅቶና ኢትዮጵያና ሕዝቧ በአንድ ላይ ሆነው እንደዱሯቸው ተበብረው፤ ተከባብረውና አንድነታቸውን አጠንክረው መኖር አለባቸው ብሎ የሚያምነው የአንድነት ኃይል ነው። ያለ ቀቢፀ ተስፋ መናገር ካስፈልገ፤ አብዛኛው ሕዝብም በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት ሳይከፋፍል ፤ በአንድ ላይ ማኖሩን ስለሚያምንና ስለሚደግፍ፤ የአንድነት ኃይሉን ዐቋም ደግፎ ቆሟል። ይህንንም በነባቢትና በድርጊት እየገለፀው ይገኛል። በጥቅላላው አነጋገር፤ ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበትን ሁኔታ በሚገባ የተረዳ ዜጋ ሁሉ፤ ሀገሪቱ አንድ ሀገር ሆና መቀጠል አላባት ብሎ ያምናል። ይህ ኃይል ደግሞ ትልቅ ኃይል መሆኑ አያከራክርም። ኃይሉን ካስተባበር በዕርግጥ ይህ የአንድንት ኃይል ፤ ዓላማውን ለመምታ የሚበግረው ተፃራሪ ኃይል ይኖራል ተብሎ አይገመትም ።

የተባበርን ኃይል የሚበግረው ተጻራሪ ባላንጋራ እንዳይኖረው ከተፈለግ ግን፤ በመተማመን ላይ የተመሰረተ የዓላማ አንድነትና ኅብረት መመስረት ወሳኝ ይሆናል። በመተማመን ላይ ተንስቶ የሚደረገ የትግል ሂደት፤ መሪና ተመሪ በመሆን ፤ ኋላና ፊት ሆኖ ለመጓዝ ጥርጣሬና ስጋት አይኖረውም። የጅቦች ጉዞ እኮ፤ ጎን ለጎን እንጅ ፊትና ኋላ የማይሆነው ፤ ጅቦች ስለማይተማምኑ ነው ። ሰበዓዊ የሆነ ፍጡር ግን ራሱን ከጥፋት ለማዳን ሲል እንኳ ተስማምቶና ተማምኖ እየታገለ ከጠቃጣበት አደጋ የማይድንበት ምንም ምክንያት ሊኖረው አይችልም። አይገባምም። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ከጥርጣሬ ነፃ ይሆናል ባይባልም፤ እናም ደግሞ፤ እንደ ይሁዳ ከሃዲ ከመሆን ይልቅ፤ እንደ ቶማስ ተጠራጣሪ መሆኑ ቢመረጥም፤ ኢትዮጵያን ከወደቀችበት አዘቅት ለማውጣት በሚድረግው ሀገራዊ ትግል ፤ ተማምኖ፤ ተስማምቶና ትባብሮ ከመታገል የተለየ አማራጭ አይኖርም። “ ጅብ ከሚበላህ፤ ጅብ በልተህ ተቀደስ “ እንዲሉ፤ በዎያኔ ዘረኛ መርዝ ከመጥፋት በፊት ዎያኔን አጥፍቶ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ማዳን የኢትዮጵያውያን የተቀደሰና ታሪካዊ ተለዕኮ ነው ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያምናል።

እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ውጥንቅጥና ውስብስብ፤ ጥልቅና የተለያዩ ችግሮች ያላባትን ሀገር ለመታደግ ፤ የዜጎቿ ተባብሮ መቆም ዋሳኝ መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጿል። ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች፤ ሊኂቃንና አገር ወዳዶች ጽፈዋል። ተናግረዋል። የሀገራቸውን ውስብስብ ችግር አስቀድመው በጥልቀት የተረዱት ታጋዮችም ብርቅ ህይወታቸውን ገብረዋል። እስካሁን ግን የሀገሪቱ ችግር መውገዱ ቀርቶ እንዲያውም ሊቀረፍት እንኳን አልቻለም ። ይባስ ተብሎም ከነአካቴው የሀገሪቱ ጨገሬታ በአስጊ ደርጃ ላይ ይገኛል ። አንዳንድ የጨነቃቸው ወገኖች ፤ የሀገሪቱን ችግር ፈረንጅ የፈታልናል ብለው ላይና ታች ሲሉ እንታዘባለን። በእኛ ዕምነት፤ የሀገራችንን ሁለንትናዊ ችግሮች ለመፍታት፤ ከኛው ከራሳችን
3

ከኢትዮጵያውያን የበለጠ መዳህኒት አለ አንልም። እረ ለመሆኑ፤ የሀገራችንን ችግር እኛው እራሳችን መፍታት ካልቻልን፤ እንዴትስ ባዕድ ይፈተዋል ተብሎ ይታሰባል ?
የሀገራችንን ችግር እኛው መፍታት አላብን ሲባል ፤ እንዲያው ለይስሙላ አባባል ብቻ ተብሎ ሳይሆን፤ ወይም ደግሞ፤ ለመፈክር ማሳመሪያና ለሠልፍ ጥሪ ማስታዎቂያ ሳይሆን፤ በእርግጥ እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ-ወክፍ የመፍተሄው ፍለጋ አካልና አምሳል መሆን አለበት ለማለት ነው። የሀገሪቱ ችግር የግል ሰዎች፤ ቡድኖችና ክፍሎች ችግር ብቻ ሳይሆን፤ የመላው ሕዝብ የጋራ ችግር ስለሆነ፤ ሁሉን አሳታፊ መፍተሄ ፍለጋ ፤በተቀነባበረና በተዋሃደ መንገድ ሊካሄድ የግድ ይላል። ሌላው ቢቅር፤ የአንድነት ኃይሉ መተባበርና በአንድ ላይ መቆም፤ የኃይል ሚዛኑን በአውንታዊ ገጽታው ወደ እርሱ ጥንካሬ ሊለውጠው ይችላል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፤ ሚዛኑ ወደ ጸረ አንድነት ቡድኖች ከደፋ፤ እነኝህ ኃይሎች ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ የሚገድባቸው ኃይል ላይኖር የችላል ብሎ መገመት የብልሆች ማስጠንቀቂያ ነው ። እንዝህላልነት፤ ለማንም ለምንም አይጠቅምም ። የዓለም ፖለቲካ ደግሞ ኃይል ወዳጋደለበት እንድሚያዘነብል በተደገገሚ የተየ ጉዳይ ነው ። የጸረ አንደነት ኃርሎች ጉባዔ ሊውስነው የሚችለው፤ ሀገራችንን ለጉዲፈቻ ለማቅረብ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ቅርጫ ስጋ ለመቅራመት ጭምርም በመሆኑ፤ የአንድነት ኃይሉ የበይ- ተመልካች ሆኖ ይቀራል ብሎ መገመት አግባብነት ይኖረዋል። ይህንን ለመጠርጥር ደግሞ በ1981 የሎንዶኑን ጸረ- ኢትዮጵያ ጉባዔ እያንገፈገፍንም ቢሆን ለመጥቀስ እንገደዳልን ። በዕርግጥም ዛሬ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚታገለው የአንድነት ኃይል የተጠናከረ በርታትና ጉልበት አለው ብሎ ገላን ሰድዶ መናገር ከማይቻልበት ደርጃ ተደርሷል። ይህንን ሃቅ ተገንዝቦ፤ ኃይሉን ማጠናከር ከምንም በላይ ሊታሰብበት ይገባል። ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያን ኅልውና መጣበቅ፤ የአንድነት ኃይሉ የቅድሚያ አጀንዳ መሆን ይገባዋል ተብሎ ከታመነበት፤ በሚከተልቱ ዐውደ ሃሳቦች ላይ መተኮር እንዳለበት የሚያጥያይቅ አይሆንም። እነርሱም፥

1. የአንድነት ኃይሉ በአስችኳይ ተሰብስቦ ኅብረት መፍጠር ፤ የዋል ይደር የሚባል አይደለም።
2. ይህ ከተከሰተ ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሙሉ ትብብርና ድጋፍ ማግኘቱ እውን ይሆናል።
3. ወዳጅና ጠላትን ለይቶ ማወቅ ለሚፈጠረው ኅብረት ወሳኝ ሚናን ይጫዎታል።
4. ለአልፉት ሃያ ሶስት ዓምታት በሀገራችን ላይ መዓተ- ፍዳ ያመጣውን ዘረኛ ሥርዓት ማስወገድ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነገር አይደለም።
5. ወኔን ማስውገድ ብቻ ሳይሆን፤ ከአሁኑ፤ መተኪያውን ማዘጋጀት፤ የትግሉ ማዕከላዊ አጃንዳ ሊሆን ይገብዋል። አሮጌ አምባገነንን አስወግዶ በአዲስ መዳፍ ለሚረግጥ አምባገነን ከመገዛት ለመዳን፤ አስቀድሞ ብልሃቱን ማዘጋጀት፤ የኢትዮጵያን መከራ ወድ ከርሰ- መቃብሩ ለመስደድ ይጠቅማል።
6. የኢትዮጵያ ሀገራዊ ልዕልና፤ የግዛት አንድነት፤ የዜጎቿ እኩልንትና ነጻነት፤ የኅበረቱ ማዕከለዊ ዕምነትና ትኩረት ግዴታ መሆን ይኖርበታል።
7. ኃይሉንና ጉልበቱን አስተባብሮ የተፈጠረ የአንድነት ኃይል፤ የመላውን ኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ ስለሚያገኝ ፤ ሀገሪቱን ለማዳን ዋስትና አለው ።
8. ይህ ዕውን ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያን ኅልውና ማስከበር ይቻላል። ሀገራችንም ለጉዲፈቻ አትዳረግም ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: