Ethiopian news and information update

ከመላኩ ይስማው

(Read in Pdf)

ሰለነኝህ ሶስት ወዶ ገቦች መፃፍ ከመጀመሬ በፊት “እንደሰራ አይጨርስ?!” ስል ልቦናዬ መልሶ “ዱሮስ መቼ የተሰሩ ሆነው!?” አለና ጠየቀኝ። እውነትም … ማዕረግ ደርድረው ከሙያቸው ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉ/የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎችን ሳስብ፣ የአንድ ወዳጄ ቀልድ ትዝ ይለኛል። ያ ወዳጄ በክፋቱ በጣም የሚጠላውን ሰው ስም እጥራና የአባቱ ስም ማን እንደሆነ እጠይቀዋለሁ። ኮስተር እና ቆጣ ብሎ ያለኝ “ለመሆኑ አባት አለው እንዴ?” ነበር። የአንዳንዶቹ ማዕረግ ባለቤት አለው ወይ የሚያሰኝ ነው።

የወያኔ 23 ዓመት ውዳቂና ጸረ ሕዝብ አገዛዝ ካደረሳቸው ከፍተኛ ጉዳቶች አንዱ ምሁር የተባለውን ክፍል ማቆሸሹና ለዚህም ክፍል አባሎች ዝቅጠት አበረታች ሆኖ መገኘቱ ነው። ወያኔ ራሱ እንደ ድርጅት የዚሁ ዝቅጠት ምልክትና ነጸብራቅ መሆኑ የሚካድ አይደለም። ምሁሮች የነበሩትን ስርዓቶች በጋራ ታግለው በኢትዮጵያዊነት መፍትሔ ሊሰጡ ሲዋደቁ፣ ወያኔን ሆነ ሌሎች ጠባብ ድርጅቶችን የመሰረቱት ደግሞ ዘረኝነትን መርጠው፤ ግንጠላን አቀንቅነው፣ ለሀገር ጥፋትና ለኋላ ቀርነት ቆሙ። ዛሬም ይኸው ችግር አልለቀቃቸውም። በመሆኑም አወቅን ተማርን ብለው ሲኮፈሱና ለሕዝብም አወቅንልህ ብለው ራሳቸውን ሲያስገምቱ፣ ምሁር በአፍንጫችን ይውጣ ባዩ ዜጋ ቁጥር መጥቋል። መማር ለማወቅ ሳይሆን ለምደንቆር ነው እንዴ የሚያሰኝ፣ የሚያስጠብብ ክስተት ፈጥረዋል። ቤትና ሕንጻ — መንገድ ስሩ ቢባሉ ፖለቲካ ሰሪ ነን ብለው ትግልን የጎዱና እየጎዱ ያሉ ሶስት ኢንጂነሮችና ሌሎች ፕሮፌሰር ዶክተር በሉን ባዮችን ማንሳቱ በቂ ምስክር ነው።

በቅርቡ ሶስት ምሁሮች (አራተኛው ፕሮፌሰር ተኮላ በትግሬ የበላይነት የናወዘና ባገኘው ዕድል ሁሉ በአጼ ምኒሊክና በአማራው ላይ የሚዘምት ነው ) ሳይጠሩት አቤት እንዲሉ የወያኔን የትልቅ ግድብ እቅድ ደጋፊ ሆነው ግብጽን በማውገዝ ከታትበዋል። ፅሁፋቸው ከዋና ዋናዎቹ ጥያቄዎች አንጻር ባዶ ሊባል የሚገባው ሲሆን፣ ምሁሮቹ–በወያኔ ቀደም ሲል አልታሙምና–ምን ነካቸው ማሰኘቱ አልቀረም። ዶክተር ሚንጋ ነጋሽ (ደቡብ አፍሪካ) በሰብአዊ መብትና ፖለቲካ ጉዳይ ወያኔን በአሉታዊ ሲተቹ ቆይተዋል። ዶክተር ማሞ ሙጬም በአንድ ወቅት ለቅንጅት ድጋፍ ሲሰጡና መጣጥፎችም ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ከዚያም በፊት ወያኔ ወደ አምቦ ሲቃረብ ለንደን ውስጥ ከጥቂት ሰዎች ጋር ስብስብ አቋቁመው፣ ወያኔና ሻዕቢያ በኦነግ አጃቢነት ሰኔ 1983 ላይ ካዘጋጁት ጉባዔ ተብዬ ጋር በተያያዘ በዚያው ስብስብ ስም በግላቸው የፃፉትን ደብዳቤ አይረሱትም። ያገኙትንም መልስ ጭምር። ዶክተር ሀሰን ሰይድ በበኩላቸው በኤኮኖሚው መስክ ሲጽፉ ያወቅናቸው ናቸው። ሶስቱም የከርሰ ምድር፤ የውሀ ወይም የግድብ ሙያ መስክ ሊቆች አይደሉም። የወያኔ ተሓድሶ ተብዬ እቅድ ደግሞ በኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃም ውግዘትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል። ወደ ፖሊቲካ የመጣሁት በ1997 ዓ.ም. ነው ያሉት ፕሮፈሰር አለማየሁ ገብረማርያምም የነጭ ዝሆን ዕቅድ (ዋይት ኤሌፋንት–ማለትም የጉራና ብዙውን ጊዜም ተጀምሮ የማያልቅ) ብለው በተገቢው ሰይመውታል።

የተሓድሶ ግድብ እቅድ በመሰሪው መለስ ለምንና መቼ እንደቀረበ ብዙዎች የተቹበት ጉዳይ ነው። ግድቡ ይመሰረትበታል የተባለውንም የጉባ አካባቢ ሶስቱ ምሁሮች የሚያውቁት አይመስልም። ለማንኛውም ግድቡን በተመለከተ ግብጽ ላይ ቡራ ከረዩ ለማሰማት፣ በተወሰኑት ምሁሮች የቀረበው ጽሁፍ ወዶ ገባ አሰኛቸው እንጂ ብሔራዊ ድጋፍን የሚያስገኝላቸው አልሆነም፤ አያስገኝላቸውም። መጠየቅ ያሉባቸውን ጥያቄዎች አልጠየቁም ወይም አንስተው ማብራሪያ አልሰጡም። ወያኔን ከግብጽ ጥቃት ለመከላከል የተጻፈ የሚመስል ጽሁፋቸው፣ ግብጽን ከማጥቃት ሌላ የግብጽንም መሰረታዊ ስጋት ሆነ የግድቡንም አጠያያቂ ይዘትና አንደምታ በተገቢው አልተቹም። ለዚህ ጽሁፍ የሶስት ምሁሮች አንጎልና ብዕር ትብብርን መጠየቁ ራሱ የሚያስገርም ነው። “ከዓባይ በፊት የወያኔ ፀረ-ኢትዮጵያ የዘረኝነት ፖሊሲ ይገደብ!” የሚለው ዐብይ ጥያቄ እና ከሁሉ ቀዳሚነት፣ እንደምን ለነኝህ ሶስት “ምሁራን” ድምር ግንዛቤ እንዳልታዬም ይገርማል። ሕዳሴ ግድብ የተባለውና የመለስ ግድብ ሊባል ታስቦ የነበረው ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ ለመሆን የተዘጋጀ ነው። ይህን በተመለክተ ግብጽ ይህን አለ አላለ ሳይሆን ዋናው ጥያቄ እውንስ ግድቡ በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊና አንገብጋቢ ነውን የሚል ነው። ግድቡ፡

  1. ከ4.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል ተብሏል። ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ማለት ነው። ይህ ገንዘብ ከየት ይመጣል?
  2. ያሉት ግድቦች ለኢትዮጵያ ፍጆታ በቅተው፣ ለሽያጭም ማቅረብ ይችላሉ እየተባለ ዛሬም በአዲስ አበባ ሳይቀር መብራት በፈረቃ መሆኑ ምን ይባላል?
  3. ሕዳሴ ግድብ በተባለው አቅም ደረጃ ከተጠናቀቀ ወደነ ግብጽ ፈሳሹ ውሃ አይቀንስምን?
  4. ወደ ሱዳን ድንበር ተጠግቶ ግድብ መስራቱ ከጥበቃ አንጻር ስህተት አይደለምን?

የሕዳሴ ግድብ ተቃውሞ የሚያስነሳው ከግብጽም ብቻ ሳይሆን ከዜጎችም ነው። ኢትዮጵያ ግድብ መስራት የለባትም የሚለው የባዕዳን አቅዋም ተቀባይነት ባይኖረውም፣ በአሁኑ ጊዜ ባለው ሁኔታና የህዝብ አቅም የተነሳ ወቅታዊና አንገብጋቢ ስምሪት ነውን ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነበር። ግብጽ ያላትን አቅዋም ባንደግፍም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ መጣሯን የምንረዳው ነው–ከከሀዲው ወያኔ ውጪ ብዙዎች የሀገራቸውን ጥቅም አስልፈው አይሸጡምና። ለዚህም ወያኔ በተንኮሉ ነገር ዓለሙን ውል አሳጥቶ ግድብ መስራት መብታችን ተነፈገ በሚል ሕዝብን በብሔራዊ ስሜት (ወያኔ በሌለው) ሊያስነሳና ግብጽን ጠላት ሊል ቢል ቢጥርም (የግብጽን ፋብሪካና ወርቅ ፈላጊ የተባሉ ኩባንያዎችን በባሕር ዳርና ቤኒ ሻንጉል ተንቀሳቀሱ ብሎ ፍቃድ ሰጥቶ!) በዚህ ወያኔ በቀደደው ቦይ ገብቶ መፍሰሱ ከምሁሮቹ ከቶም ባልተጠበቀ ነበር። ተከዜ ግድብ፤ ጣና በለስ ግድብ፤ ግልገል ጊቤ ቁጥር 1፤ ሁለትና ሶስት ወዘተ ግድቦች ሁሉ በቂ ሀይል የሚያመነጩ ናቸው። ያሉት ያመነጩትን ሀይል ወደ ከተሞች ማድረስ ያልተቻለውም የቻይና ኩባንያ ጉቦ ሰጥቶ መስመር የመዘርጋቱን ኮንትራት ስለወሰደና ይህንኑ አለማክበሩ ብቻ ሳይሆን የሚተክላቸውም ትራንስፎርመሮች ሲተከሉ በ አጭር ጊዜ የሚፈነዱ መሆናቸውን በማውቅም ነው፡፡ ለዚህም ነው በ80 ቢሊዮን ብር ግድብ ለመስራት ከመፍጨርጨር ያሉትን በሳራ ላይ ለማዋል ማተኮር ይሻል ነበር የሚባለው። እኔ የምሞት ዛሬ ማታ፣ እህል የሚደርስ በልደታ ነው ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር– ችግሩ ዛሬ፤ ችግሩን ይፈታል የሚባለው ግድብ ደግሞ የሚደርሰው ገና ከሰባት ስምንት አመት በኋላ ያውም ከተሳካ።

ዋናው ጥያቄ እዚህ ላይ ይነሳል — ወዶ ገባዎቹ ሚዛንና ክብደት ባይሰጡትም። በምን አቅም ነው የሚሰራ ይህ ግድብ? ረሀብ በሚያጠቃት ሀገር፤ የኑሮ ውድነት ሕዝብን በደቆሰበት ሀገር፤ ከናይጀር ብቻ የምትሻል ድሀ በተባለች ሀገር፤ ድሀው ሕዝብ በግድ ገንዘብ አዋጣ ተብሎ ተሰንጎ ተይዟል። እስረኞች ሳይቀሩ አዋጡ ተብለው ተይዘዋል። ነጋዴውና ከወያኔ ግልጋሎት ፈላጊው ሁሉ አምጣ ተብሏል። ድሀ ህዝብ 80 ሚሊዮን አዋጥቶ ግድብ ሊሰራ አይችልም። ገጣሚው እንዳለው ቦንድ የተባለውን “ቡዳ” ማለትም ወያኔ የሚባል ተምች በልቶታል። ለምን ዘራፊው ወያኔ ከዘረፈው ገንዝብ መዋጮ አያደርግም? ሕዳሴ ግድብ ዳግም ሕዝብን የመዝረፊያ ስራ ነው። ምሁሮቹ ያዋጡ አያዋጡ ባላውቅም የወያኔን ዝርፊያ ቦታ የሰጡት አይደሉም። ለመሆኑ ግድቡ ምን ያህል ሀይል ያመነጫል? ስንት ዜጋ ከዚያ ቦታስ ይፈናቀላል? ከበፊቱ ስምሪቱስ ይደናቀፋል ወይ ለውጥ የለውም? ይህ ሁሉ ወዶ ገባዎቹን ያስጨነቃቸው አይመስልም። ትኩረታቸው ግብጽ ላይ መጨፈርና ወያኔ አይነካ ላይ በመሆኑ። ማንም ሀገር ወዳድ ማወቅ ያለበት ግን የወያኔ ፍላጎትና የኢትዮጵያ ጥቅም ሁሌም ተጻራራ መሆናቸውን ነው። ወያኔ ተጨፈኑ ሳይላቸው በራሳቸው ዓይናቸውን ጨፍነው መሞኘትን ብልህነት ብለው የወሰዱ ምሁሮች ግን ነጋ ጠባ ያሳፍሩናል። ሰማይ ከመሬት ቢጋጠም ግን የኢትዮጵያ ብሐራዊ ጥቅም ሁሌም ከወያኔ ጥቅም ጋር የተጻረረ ነው። ወያኔ ብሔራዊ ሲል ኢትዮጵያ ማለቱ ሆኖ አያውቅም። በዚህ ሕዝብን አስጭንቆ አዋጡ በሚለው የዝርፊያ እርምጃ ምክንያት ብቻ ግድብ የተባለውን በአሁኑ ጊዜ ማውገዙ በተገባ ነበር።

ግብጽ ስግብግብና የአባይ ወንዝ ተፋሳሽ ሀገሮችን ጥቅም ጉዳዬ ሳትል ራሷን ብቻ ማስቀደሟ የሚወገዝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ግድቡ ሲጠናቀቅ ሰው ሰራሽ ሀይቁን/ግድቡን ለመሙላት የሚፈጀው ጊዜና የፈሳሽ ውሃውን ልክም መቀነሱን ተኮናታሪው ሳልኮስትም አልደበቀም። ትላልቅ ግድብ መስራት ደግሞ ከቻይና እስከ ጊቤ 3 የአካባቢውን ነዋሪና የአየር ሁኔታ እንደሚጎዳ ፖለቲካ የሚዋሱ ሳይሆኑ ዓዋቂዎች ያረጋገጡት ነው። ከዚህም አንጻር ሕዳሴ ግድብ ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። ግድቡ ሀይል አመንጭቶ ገዘብ ቢገኝስ ይህ ለወያኔ ነው ለኢትዮጵያ። ሞኞች የአየር መንገዱ ገንዘብ የወያኔን ካዝና እየሞላ ሳለ ለኢትዮጵያ ነው ጥቅሙ ብለው ሲከራከሩ ታዝበናል። ስለ ሕዳሴው የሚነገረው ውዳሴ ከንቱ ነው።

ከግድቡ አነዳደፍ፣ አገነባብ እና ከተጠናቀቀም በሁዋላ ተጠቃሚው ማነው ከሚለው ጥያቄ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ግን አሁንም “ከዓባይ በፊት ዘረኝነትን መገደብ” የኢትዮጵያዊያን ሀገር ወዳዶች ሁሉ የመታገያ መሪ መፈክር መሆን አለበት። እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1936 ጣሊያን ሀገራችንን በቋንቋ መስመር ከፋፍላ የነደፍችውን ሰነድ ከአቧራ አንስቶ ተግባራዊ በማድረግ፣ ወያኔ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ቀስ በቀስ ለመግደል፣ በትረ-መንግሥቷን ይዞ እየገዛት ነው። በአጭር ጊዜ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ጥገት ቢገዙም፣ በወያኔዎቹ መሪዎች ልቦና ያለችው እና በረጅም ጊዜም እየገነቧት ያለችው ሀገር ታላቋ ትግራይ ነች። ከዚያ ውጭ ያለው እና በየቋንቋው አጥር ተሠርቶለት የተመሠገው ወገን ነገ እርስ በርሱ ሊያስተራርዱት እያዘጋጁት ያለ ነው። ብሔራዊ የወል እኔነት እንዲጠናከር ከሚያስፈልጉት ጉዳዮች ውስጥ፡ ብሄራዊ አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ፣ ነፃ የጉልበት (የሠው ሃይል) እንቅስቃሴ፣ የአደጉ የምጣኔ ሀብት፣ የትራንስፖርት እና የህዝብ መገናኛ ብሄራዊ መረቦች የሚጠቀሱ ናቸው። ታዲያ ከዚህ አንፃር በወያኔ እየተገፋበት ያለው ፖሊሲ ወደዬት እየወሰደን ነው? እንኳንስ የበለጠ መዋሃድ ሊከሰት፣ ያለነው ወደዬቋንቋ ጋጣችሁ ተሰባሰቡ እየተባልን አይደለም እንዴ? ለመሆኑ በዚህ ጋጥ ያልተፈረጀ/ለመፈረጅ ቢፈልግ መብቱ የሆነ ወገን ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖር መብት አለው? ከወያኔ ፓስፖርት/መታወቂያ/ሌላም ሰነድ ማውጣት የሚፈልግ ማንኛውም ወገን እራሱን የግድ ከአንድ የቋንቋ ጋጥ (እነሱ ብሄር፣ ብሄረሰብ ብለው በሰየሙት) መወገን አለበት። ሩዋንዳዊያንም እርስ በርስ ከመተላለቃቸው በፊት የነበረው አገዛዝ ተመሳሳይ ፖሊሲ ያራምድ ነበር። እናም በዘር ለመተላለቅ የቡድን መለያው ቀድም ብሎ ተዘጋጅቶላቸው ነበር። የዘር ፖለቲካን ሳስብ “የዮግዝላቪያ ሞት” ለሚለው መጽሐፍ ፀሐፊ ቃለ-መጠይቅ የሰጡ የሀገሬው ዜጋ የቲቶን ሞት አስመልክቶ ያሉት ነው ትዝ የሚለኝ። ቲቶ የተቀበሩ ዕለት የተሰማቸውን ሲገልጹ እንዲህ ነበር ያሉት፡ “ያን ዕለት ያለቀስኩት ለቲቶ ሞት ሳይሆን ለዩግዝላቪያ ሞት ነበር!” እኛም ብዙ ቲቶዎችን፣ ብዙ ብሄራዊ ጀግኖችን በድቅድቅ ጨለማው ውስጥ በአውሬዎች – ወያኔ በሚባሉ አውሬዎች – እያስበላን፣ የብሄራዊ ህልውናችንን መብራት እስከጭራሹ እንዳናጣው እፍራለሁ። እነማሞም ኢትዮጵያ በሚሄዱ ጊዜ በያዝኩት የውጭ ፓስፖርት ሳይሆን በኢትዮጵያ መታወቂያ የምንቀሳቀስ ቢሆን ኖሮ ብለው ቆም ብለው ቢያስቡ ጥሩ ይመስለኛል። በኢትዮጵያዊነት፣ አልፎም በሚያቀነቅኑት ፓንአፍሪካኒዝም ላይ የተቀሰረው ጦርም ይታያቸው ይሆናል።

ኢትዮጵያዊነት እንዲህ በቀላሉ የማይጠፋ፣ የማይተን ሆኖ ነው እንጂ እስከዛሬም የተዋለበት ቀላል አይደለም። ወያኔ የሚያራምደውን የዘረኝነት ፖሊሲ ጦስ ምልክቶች እያየነው ነው – ያሳለፍናቸውን 23 ዓመታት ልብ ካልን። በረጅም ጊዜ ታሪክ፣ በፍቅርም በጦርነትም፣ በለቅሶም በሠርግም፣ በመውለድ በመግደልም በወዘተ ወዘተ የተገነባው ኢትዮጵያዊነት እየታገላቸው እንጂ፣ እየገዙን ያሉት የወያኔ መሪዎች ቅንጣትም ብሄራዊ ስሜት የላቸውም። ይህን ብሄራዊነት፣ ኢትዮጵያዊ ብሄራዊነት የሚያሳዩን ለአጭር ጊዜ ፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ነው። አለዚያማ እስኪ ምን የፖሊሲ ማሻሻል አድርገዋል? ለአጭር ጊዜ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ መግዛት፣ በረጅሙ ሌላውን አካባቢ በታትኖ እና የመተላለቂያ ቦንብ አሲዞ ማባላት፣ ራሷን የቻለች ታላቋን ትግራይም የመጨረሻው የማይታጠፍ ግብ አድርጎ መጓዝ ነበር ዓላማቸው፣ አሁንም ነው።   ታዲያ ለአጭር ጊዜ አቅጣጫ ማስቀየሪያ፣ ማዘናጊያ እንዲሆነው አስቦ፣ ምንም ይሁን ምን ቢሰራ፣ ሀገር የሚያፍራርስ ጠላት እንዴት ቸል ይባላል። ምነው ሶስቱ ምሁራን፣ ሶስቱ ? ? ? ሆናችሁ ሰውን ግራ አታጋቡ እንጂ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: