Ethiopian news and information update

Ethiopia and the Horn – Commentary (Read in pdf)

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ፡   ዋሾው የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያን ከዓለም ሀብታም ሀገሮች 67ኛው አድርገናታል ሲል ቅንጣትም ሀፍረት የሚሰማው አይደለም። ስለ ሰላምም የሚያወሳው የተለየ አይደለም። በ አፍሪካ ቀንድ ሰላም አለመስፈኑ ብቻ ሳይሆን የባሰ ጦርነት ጥሩምባ እየተነፋም ነው ማለት ይቻላል። ወያኔ በሶማሊያ ያስገባውን ጦሩን በዚያ ባለው የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ አንድነት ማህበር ጦር ተቋም ውስጥ ማስገባቱ በራሱ የዚያችን ሀገር ችግር የሚያባብስ መሆኑ ለወያኔ እንጂ ለሁሉም ግልጽ የሆነ ነገር ነው ። በኢትዮጵያ የወያኔ አገዛዝ ቀውስና ብጥብጥን እንጂን ሰላምና መረጋጋትን እንዳላሰፈነ ደግሞ የአደባባይ ምስጢር ነው ።

እስቲ የአካባቢውን ሁኔታ እንዳሰው ። በቅድሚያ የሶማሊያን ሁኔታ ብንመረምር ወያኔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሳይሆን የአሜሪካንን እዝ ለማስፈጸምና ገንዘብና ድጋፍንም ለማግኘት ሲል በተደጋጋሚ በሶማሊያ ላይ ወረራ አካሂዷል፤ ወታደሮችንም አስጨርሷል፤ በሶማሊያ ሕዝብም ላይ የመብት ረገጣ  አካሂዷል ። ጦር ወደ ሶማሊያ መላክ የአያዋጣ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ በጥቅም የታወረው ወያኔ ግን (ብዙ ገንዘብ አግኝቶበታል፤ አዛዥ ጄኔራሎቹም ከብረውበታል) ዘው ብሎ ያተራምሳል ። በሶማሊያ ያለውን የአፍሪካ ጦር ስብስብም በቅርቡ ተደባልቆ (ከ 4000 በላይ ወታደር ማለት ነው)  በጸረ ኢትዮጵያነት አማጽያኑ እንዲጠናከሩ አስተዋጾ እያደረገ ነው ። ለድምሰሳ የታጨው ዓል ሸባብ የተባለው አክራሪ ቡድን የተዳከመ ቢሆንም አሁንም በሞቃዲሾ ቦምብ እያፈነዳና ጥቃትም እያደረሰ ለመሆኑ በየሳምንቱ እየታየ ነው ፡፡ ወታደር ቁጥር ይጨመር የሚለው ጫጫታ አሁንም እየተሰማ ነው ። ዛሬ በባዕዳን  ጣልቃ ገብነት የተባባሰው የሶማሊያ ሁኔታ ሲጀምርም የራሷ የሶማሊያ የፖለቲካ ችግር ያለበት ቢሆንም በባዕዳን ጣልቃ ገብነት ድብልቅልቅ ማለቱ የሚካድ አይደለም። ደርግ የዚያድ ባሬን አገዛዝ ጠላት ብሎ በመፈረጅ ተቃዋሚዎቹን አደራጅቶና አስታጥቆ በማሰማራትና እርስ በርሳቸውም እንድያብሩ በማገድ ለዚያድ መውደቅ ብቻ ሳይሆን ለሶማሊያ መንግስት አልባነትም የማይናቅ ሚና ነበረው ። የአካባቢው ሁኔታም–ሻዕቢያን ወያኔ ግጭት፤ የቃታርና ሳውዲ ሚና፤ የግብጽ ፍላጎት ፤ የአሜሪካ ጸረ ሽብር ተብዬ ዘመቻ ወዘተ ሶማሊያ ከጦርነትና እርስ በርስ ብጥብጥ ነጻ እንዳትሆን አግዷታል ። ይህም ሁኔታ በኦጋዴን ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ ማድረጉን ቀጥሏል ። ሰላም በኢትዮጵያ የሚለው ጥያቄ የሶማሊያን ሁኔታ በእይታው ማስገባቱ የግድ ነው ።

ከወያኔ ጋር አብሮ ያለው የጅቡቲው መሪ ኦማር ገሌ ሀገሩን ለፈረንሳይ የጦር ሰፈርነት ሸጦ ከከረም በኋላ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ለሞኒየር የተባለውን የቅድሞ የፈረንሰይ ጦር ሰፈር ለአሜሪካ ሸጦ 4000 በላይ የአሜሪካ ወታድሮች ሰፍረዋል ። በአርባ ምንጭ ወያኔ እንዳደርገው ሁሉ የአሜሪካ የ አየር ሃይል ሰፈርም ተመስርቶ ነጂ አልባ ተዋጊ አይሮፕላኖች (ድሮኖች) እያበረረ ሶማሊያንም የመንንም በመድብደብ ላይ ነው ። ጅቡቲ ራሱ የአፋር ተቃዋሚዎች (ፍሩድ) በትጥቅ ትግል እያጠቃው በመሆኑ ና አምባገነናዊ አገዛዙም አፋሩንም ኢሳውንም እያበሳጨና እያስቆጣ ያለ በመሆኑ የአገዛዙ ዘመንም ውሱን መሆኑ ይታያል ። ገሌ ለአሜሪካ መሳሪያ በመሆኑና በሶማሊያም ከወያኔ ጦር ጎን ( ሰፈር 4 በሚባለው)  ያሰማራ በመሆኑ የአል ሸባብም የጸረ አሜሪካን ሀይሎችም ሁሉ ተጠቂ መሆኑ የሚጠበቅ ነው። ይህ ደግሞ መዘዙ ኢትዮጵያንም የሚነካ መሆኑ መታውቅ ያለበት ነው ። ለገሌና ሚስቱ ወያኔ ለም መሬት መስጠቱ መረሳት የለበትም ። ዕድሜ ለወያኔ ኢትዮጵያ በጦርነት ተዘፍቃለች፤ በጦርነት ተከባለች፤ ጠላቶች ሸምታለች።

ምዕራባውያን የሱዳኑን የበሺር አገዛዝ ለማዳከም በሚል ፍትሓዊነቱ አጠራጣሪ ሆኖ ለማያውቀው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ትግል ድጋፍ ቢሰጡም የደቡቡ መሪ ጆን ጋራንግ የተባበረች አዲስ ሱዳን ይል የነበረው ስላልጣማቸው ጋራንግን በሄሊኮፕተር አደጋ ሽፋን አስገድለው የግንጠላን ኣቀንቃኞችን የበላይነት በማስፈን ደቡብ ሱዳንን ሊገነጥሉ ቻሉ። በማሊና መካካለኛ አፍሪካ እንደታየውም የቀውሱ መሰረት የኤኮኖሚ ጉዳይ ነውና (ደቡብ ሱዳንንን በተመለከተ ቤንዚንና ለም መሬት፤ ማሊና መካካለኛ አፍሪካን በተመለከተ ለኑክሌር ቦምብ አስፈላጊው ዩራኒየም፡ ወዘተ) በደቡብ ሱዳን የቻይና፤ፈረንሳይ፤እንግሊዝና አሜሪካ ፉክክር ሳይውል ሳያድር ተከሰተ። ደቡብ ሱዳናውያንም ሰሜኑን/የበሺርን አገዛዝ በመዋጋት ዴጃ የተወሰነ ደረጃ ትብብርን ቢያሳዩም በትግሉም ጊዜ ያመሳቸው የ ጎሳ ልዩነት ሳይረሳ፣ ሀገር ሲባሉም ቀጥሎ የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ስሜት የሚለውን ከመጠንከር አግዶትና ሁኔታውም በሙስናና ዋልጌ አገዛዝ ታጅቦ ለዛሬው የርስ በርስ ጦርነት በርን ከፍቷል ። አማጺው ቡድን በኑዌሩ ሪያክ ማሻር ሲመራ መንግስት ነኝ ባዩ ወገን ደግሞ በሳልቫ ኪር ከዲንካው ቦር ጎሳ ይመራል ። ዲንካው ብዙሃን ቢሆንም ራሱ በዲንካ ቦር (ኪር)ና በዲንካ ባህር ኤል ጋዛል (ጋራንግና ሚስቱ)  የተከፋፈለ መሆኑ ችግሩንን ኣባብሶታል ። በወያኔ ፈር ቀዳጅነት የጎሳ ፖለቲካ አፍሪካን ለማዳከም ጠቃሚ ነው ተብሎ በአሜሪክና ሌሎቹም መገፋቱ ምን ያህል ጉዳት እያደረሰ መሆኑ የሚታይ ነው ። የደቡብ ሱዳን ይዘት በተለይም ከጋምቤላ ጋር በተያያዘው የመሬት ሽያጭ ና ቀውስ ጋር ተያይዞም መገምገም ያለበት ነው ። ማለትም ከሕዝባችን ትግል ጥቅሙና ጉዳቱን በማመዛዘን ። ባዕዳን ሱዳንን ለማንበርከክ የዳርፉርና የኮርዶፋንንም እንቅስቃሴዎች በመደገፍ ላይ ናቸው ። ምንም እንኳን ወያኔ መሬታችንንም አሳልፎ እየሰጠ ቢሆንም ሱዳንን/በሺርን አቅፎ ለመቀጠል ያደረገው ጥረት እስካሁን የሰራለት ቢሆንም ከግብጽ ጋር በጀመረው ንትርክ የተነሳና ከበሺር ራሱም ይወገድ አንጻር በዚህ ጎኑም ችግር ሊመጣበት የሚችል ነው ። ዩጋንዳም የራሷ አሮባት በሶማሊያም ሆነ በደቡብ ሱዳን የምታደርገው ጣልቃ ገብነት መዘዙን ያበዛዋል ።

በዚህ ሁሉ የቀውስ ሁኔታስ ገብቶ ግን የሰጎን ፖለቲካን መርጦ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው ሊል የሚቃጣው ወያኔ ራሱ ከአሜሪካ ቡችላነት ባሻገር ከኢትዮጵያ ጥቅም አንጻር ይህ ነው የሚባል የውጭ ጉዳይ ፖለቲካ ወይም አቅዋም እንደሌለው ግልጽ ነው ። በደቡብ ሱዳን ሁኔታ በቻይና አምባሰደር የሆነው ድኩሙ ስዩም ልዩ መልዕክተኛ ተብሎ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተብየው በላይም ሲቀመጥም ለማየት በቅተናል ። ውጥንቅጥ ነው–ለወያኔ ዋናው ጉዳይ ወያኔያዊና ከፍፋይ አላማውን ከግብ ማድረስ ነው ። ሙስናና ዝርፊያ ነው ። ከወረርው ያተርፋል፤ ሰላማ አስጠባቂ እያለ ወታድር ሲማግድ ያተርፋል ። ጠቅለል ባለ መልኩ የአካባቢውን ሁኔታ ስናየው ግን

  • ጦርነቱ እየተፋፋመና ኢትዮጵያንም ሊጎዳ በሚችልበት ደረጃ እየተስፋፋ ነው
  • የሕዝቦች ድህነት እያየለ ነው። (እዚህ ላይ ሀፍረተ ቢሱ ወያኔ ኢትዮጵያን ከዓለም 67ኛዋ የበለጸገች ሀገር አደረግኳት በሚለው ሳቃችንን ቀጥለን ማለት ነው !)
  • ወያኔና አሜሪካን አረመኔውን ስርዓት ከውድቀት ለማዳን ሻዕቢያን ለማግባባት የወጠኑት ሴራም አልሰራም
  • የነሌንጮ አይታክቴ ውርደትም የወያኔ ቀውስ የሚያረግብ አይሆንም
  • በአካባቢው የአሜሪካ ፖለቲካ (የሶማሊያን የተጠሉ የጦር አበጋዞች አቅፎ ቀውሱን እንዳባባሰው ሁሉ) ሕዝቦችን የሚጎዳ ነው፤የሚቀጥለውም የባስ ቀውስ በመፍጠር ነው
  • ሰላም የለም፤ ዕድገት የለም፤ ዴሞክራሲ ጭራሽም የለም ።

ይህን ሀቅ ነው በግምት አስገብተን ትግላችንን መቃኘት ያለብን ። ሳሩን ዓየህና ገደሉን ሳታይ የሚለው ዕንዳይመጣ ማለት ነው ። ከዚህ ቀደም ከዚህ የባሰ አይመጣም ብሎ መዘናጋቱ ወያኔን በጫንቃችን ላይ እንዳሰፈረብን ማወቅና ዓለመዘንጋት አለብን ። ከወዲሁ ነገን መቃኘትና የኢትዮጵያን አንድነትና ዴሞክራሲ መስፈን ለመረጋጋጥ ማስብ፤ ማትለም መዘጋጀት አለብን ማለት ነው። ዳግመኛ እንደገና በአምባገነኖችና የባዕድ ቅጥረኞች ልንቀደምና ድልን ልንነጠቅ  አይገባም ። በአካባቢያችን ያለው ሁኔታ ሁሉ ይመለከተናል ። ያገባናል ። የሀገራችንን የነገ ህልውናና ዕጣ ይመለከታልና ። ከኢትዮጵያ ዓንጻር ሰልፋችንን ማስተካከልና የሀገራችን ጠላቶች ሁሉ ለይቶ አውቆ በስልት መታገል ትኩረታችንም ግዳጃችንም ሊሆን ይገባዋል ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: