Ethiopian news and information update

345

Comments on: "ዝምታ ለበግም አልበጃት! በዊኒፔግ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ!" (1)

 1. ለቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዊኒፔግ፣
  ከቤተ ክርስቲያኑ አማካሪ ኮሚቴ
  ሕዳር 15፣ 2005 Nov 24 2012
  በደስታ የተሞላች በፍቅር የተሳሰረችና ሰላም የሰፈነባት ቤተ ክርስቲያናችን እንድትጠናከር የምናደርገው ልፋትና ጥረት መታየት ያለበት በበጎ መልኩ እንዲሆን ከጅምሩ እንዲታወቅልን ለማሳሰብ እንፈልጋለን።
  በመጀመሪያ ይህ አማካሪ ኮሚቴ የተቋቋመዉ በቤተ ክርስቲያኒቱ አመራርና አስተዳደር ነው። እኛም ይህንን ሃላፊነት ስንቀበል፣ ለኦርቶዶክሳዊ ዕምነታችንና ለቤተ ክርስቲያናችን የድርሻችንን ለመወጣትና የሚፈለግብንን ሁሉ ለማድረግ በተሰጠን መመሪያ መሰረት የመጀመሪያውን ሪፖርታችንን አዘጋጅተን ማቅረባችን ይታወቃል። ሪፖርታችንም በሰፊ ውይይትና ጥናት የተመሰረተ ነው። በሪፖርቱ ላይ የተቀመጡት አበይት ጉዳዮች መልስ እንዲያገኙ ጠይቀን ነበር። ይሁንና እስካሁን በቂ መልስ አላገኘንም።
  ቤተ ክርስቲያናችን ከተቋቋመች ይኸውና ከ 17 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ቤተ ክርስቲያኗ እንደተቋቋመችም ምዕመናኑ በየጊዜው እየተሰበሰብን በመጸለይና እርስ በርስ በመወያየት ኦርቶዶክሳዊ ሕይወታችን ለማጠናከር ስንንቀሳቀስ ቆይተናል። በመቀጠልም በዚህ ሕንጻ የኦርቶዶክስ ሥርዓት እንደሚያዘው ከአምስት ባላነሱ ካህናት እየተቀደሰ ያምላካችንን ስም በምስጋና ለመጥራት በቅተናል። ለዚህ ያደረሰን አምላካችን ስሙ ዘወትር የተመሰገነ ይሁን።
  በአገልግሎት በኩልም ዓመታዊ በአላት በቤተ ክርስቲያኗ ደምብ መሰረት በድምቀት ተከብረዋል፣ ወንጌል በስፋት ተሰብኳል፣ የምስጋና መዝሙሮች ተዘምሯል፣ ብዙ ሕጻናት ክርስትና ተነስተዋል፤ ብዙዎች በቤተ ክርስቲያናችን ደምብ ተጋብተዋል። እንደዚሁም ብዙዎች ለተከበረውን የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ሥጋና ደም ለመቀበል በቅተዋል። ያምላካችን ፈቃድ ሁኖ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን ወንድሞችና እህቶቻችንን ደግሞ በኦርቶዶክሳዊ ሥነ ሥርዓት ሽኝት አድርገንበታል። እንደዚሁም በያገሩ በስደት የነበሩትን ወገኖቻችን ወደዚህ አገር መጥተው የተረጋጋ ኑሮ እንዲጀምሩ ቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ አስተዋጽኦና ድጋፍ አድርጋለች።
  እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁንና ባንድ ወቅት ይህች ቤተ ክርስቲያናችን በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ሌሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናት ጋር ስትነጻጸር በጣም በተሻለ መልኩ በፍቅርና በሰላም ስትተዳደርና ሰፋ ያለ መንፈሳዊ ትምህርት ሲሰጥባት፣ አልፎ ተርፎም እግዚአብሔር የተመሰገን ይሁንና፣ አንዳንድ ሰዎች ከሌላ ዕምነት ወደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እንዲመጡ ሁነዋል።
  ነገር ግን ባሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችንን አንዳንድ ፈተናዎች በፊቷ ተጋርጠውባታል። በእነዚህ ፈተናዎችና ጉድለቶች ላይ ተወያይተን ባስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘንላቸው ወደ አልተፈለገና ወደ ከፋ ችግር እንዳያደርሱን እንሰጋለን። እኛ የመማክርት ኮሚቴ አባላትም በሰፊው ለመውያየትና ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሳሳነው ይኸው ሥጋታችንና ለዕመነታችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ያለን ልባዊ ፍቅርና ቀናዒነት ነው።
  ”ጆሮ ለባለቤቱ ባዕድ” ሆነና ላስተዳደሩና ለቦርድ አባላቱ በግልጽ ባይነገርም፣ ቤተ ክርስቲያናችን በአደጋ ላይ መሆኗ በግልም በቡድንም እየሆኑ ምዕመናኑ ስለ ጉዳዩ ይጨነቃሉ፣ ያዝናሉ፣ ይጸልያሉ። ባሁኑ ጊዜ ምንም ችግር የለም፣ ሁሉም ነገር እንደነበረው ይቀጥል የሚሉት አስተዳደሩና የቦርድ አባላቱ ብቻ ይመስሉናል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለቤት የሆኑት ምዕመናን ግን መድረኩ ስላልተከፈተላቸው በግልጽ ተወያይተው ብሶታቸውን ለመግለጽም ሆነ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመጠቆም ስላልቻሉ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ብቻ የሚወያዩበት ጉዳይ ሆኗል።
  ስለዚህም ጥያቄያችን “የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና አንድነትን ጠብቀንና ከተጋረጠብን ከዚህ አደጋ አምልጠን እንዴት መቀጠል እንችላለን?” የሚል ነው። ይህን ጉዳይ እያንዳንዱ የአማካሪው ኮሚቴ ጊዜውን ሰውቶ በሰፊው አስቦበትና በጥልቀት ተወያይቶበት ለቤተ ክርስቲያናችን ሕልውና ሲባል ችግሮቹ ግልጽ መውጣትና በጊዜው መታረም እንዳለባቸው በማመን እነዚህን ችግሮች በመዘርዘር የመፍትሄ ሃሳቦችን ይጠቁማል።
  ይህች ቤተ ክርስቲያን፣ ጉዳዮችን ሁሉ እኛ እናውቅልሃለን በሚሉ ላይ ብቻ የምትተው የገጠር ቤተ ክርስቲያን አይደለችም። ምክንያቱም የምንኖርበት አገርና አካባቢ ከንደዚህ ካለ አሰራር ጋር የማይስማማ በመሆኑና ቢያንስ ቢያንስ እያንዳንዱ ምዕመን የድርጅት አሰራርን ስለሚያውቅ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ የዕመነት ቦታ ብትሆንም በድርጅት መልክ በሀገሩ ህግ መሰረት እንደተቋቋመች የታወቀ ነው።
  በተለያዩ ጊዚያት ነገሮች ”በቃለ አዋዲ መሠረት” ወይም ”ቃለ አዋዲ በሚያዘው” እየተባሉ የሚሰጡ መልሶችንም ሰምተናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቃለ አዋዲ ሰፊ መመሪያ ያለበትና እኛም ከውስጡ የምንወስዳቸው ብዙ ጠቃሚ መመሪያዎች ስላሉበት ነገሩ በጥሞና እንዲጤንበት በአንክሮ እናሳስባለን።
  በየዋህነት መልስ ሳይሰጡባቸው የታለፉ ጉዳዮች ካሉ መፍትሄው መመካከርና መልሶችን ማፈላልግ ነው። አንድ መስመር ጠማማ መሆኑ የምናውቀው ቀጥ ያለ ሌላ መስመር ሲታየን ነው። እንዲሁም መስታዎች የፊትን ቁሻሻ ያሳያል እንጂ ቁሻሻውን አያስወግድም። ሕግ የሚጣሰው ሕግ ሲኖር ብቻ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር እኒዚህን ጥቆማዎች ተቀብሎ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና እንድነት ሲባል አስፈላጊውን እርምጃ እንዲስወስድ፣ በጽሁም ላቀረብነው ጥያቄም መልሱን በጽሑፍ አንዲሰጥ በትሕትና እንጠይቃለን። ችግሮቹን ከዚህ በመቀጠል እናቅርባለን።
  1) የመተዳደሪያ ደንብ፤
  ቤተ ክርስቲያናችን ምዕመናኑ በግልጽ የሚያውቁት የመተዳደሪያ ደንብ የላትም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የመሰለ ታላቅ፤ ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ቀርቶ ማንም ትናንት የተቋቋመ ማህበር እንኳ የማህበሩ አባላት የሚያስተዳድርበት ሕግና ደንብ እንዲኖረው ግድ ነው። ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያናችን ደንብና ሕግ እንዲኖራት ከምዕመናኑ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን በቂና አጥጋቢ መልስ አልተገኘም። ሰለዚህም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ አዋዲን መሠረት ያደረገ የቤተ ክርስቲያናችን ደንብና ሕግ ባስቸኳይ እንዲዘጋጅ እንጠይቃለን።
  2) የአስተዳደር ኮሚቴ አባላት አሿሿምና የሥልጣን ዘመን፤
  በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን የመረጃ ልውውጥ እጥረት በጉልህ ይታያል። ስለዚህም ማን ለምን ተጠያቂ እንደሆነ አይታወቅም። ለምሳሌም ቤተ ክርስቲያናችን ስንት አባላት እንዳሏት፤ የቦርዱ አባላት እነማን እንደሆኑ፣ የሥራ ድርሻቸው ምን እንደሆነ፣ የቤተ ክርስቲያኗ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶች ምን እንደሆኑ፣ ቦርዱ በዓመት ምን ያህል ጊዜ እንደሚሰበሰብ፣ የሚያስተላልፈው ውሳኔ ምንና ምን እንደሆነ ለምዕመናን የተገለጸ ነገር የለም።
  በትንሹ እነዚህ ከላይ ይተዘረዘሩትን ጉዳዮች ለመፈተሽ እንኳ የመተዳደሪያ ሕግ መኖር አማራጭ የሌለው ነገር ነው።
  የሰበካ ጉባዔ ሕግ አለ ሲባል በወሬ ከመነገሩ ባሻገር አይተነው አናውቅም። በ እርግጥ ህግ ካለ ለምን ተደብቆ እንደተቀመጠ አይገባንም። ስለዚህ ይህ ሁሉ ጉድለት መስትካከል አለበት። ተጠያቂነትና ሃላፊነት የሚኖረው ሕግና መተዳደሪያ ደንብ ሲኖር ነው። ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ሃላፊነት ከሌለ የምናስተላልፈው መልእክት አወዛጋቢ ስለሚሆን ውሎ አድሮ ትልቅ ችግር እንደሚያመጣ መገንዘቡና አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዱ ጠቃሚ ነው እንላለን።

  ይህ ጉዳይ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚተው ነገር አይደለም። የሁሉም ምዕመን ጉዳይና የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና የሚመለከት ነገር ነው። ስለሆነም ምዕመናን ይመጣሉ ይሄዳሉ፣ ካህናት ይመጣሉ ይሄዳሉ፣ የቦርድ አባላት ይመጣሉ ይሄዳሉ፣ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችንን የሚይቆይልንና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላልፍ ሊያደርግልን የሚችለው የሰበካ ጉባዔው መተዳደሪያ ሕግ ሲኖር ነው። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያናችን ከተጋረጠባት አደጋ ተርፋ እንድታድግና እንድትስፋፋ የተሟላ አገልግሎትም እንድትሰጥ ከተፈለገ ይህ ማሳሰቢያችንና ጥቆማችን ልብ ሊባል ይገባል።
  ምንም እንኳ በሰለጠነውና ዲሞክራሲ በሰፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ብንኖርም፤ የቤተ ክርስቲያናችን አመራር ግን ዲሞክራሲዊ አይደለም። የዲሞክራሲ አሠራር ባለመኖሩም የኮሚቴ አባላቱ ለብዙ ዓምታት ባመራር ላይ ተቀምጠዋል። ምዕመኑ እንኳን ድምጹን ሰጥቶ ሊሾማቸው ቀርቶ መቸና በማን እንደተሾሙ፣ የሃላፊነታቸው ገደብ ምን እንደሆነ ለይቶ የማያቃቸው አባላትም በኮሚቴው አሉበት።
  ይህ አሠራር ትክክል ባለመሆኑ አሁን ያለው ኮሚቴ ፈርሶ የኮሚቴ አባላት ሁሉ በምዕመናን ሙሉ ተሣትፎ እንዲመረጡ፤ የሥራ ሃላፊነታቸውም ተዘርዝሮ እንዲነገር። ያገልግሎት ዘመናቸውም የቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ደንብ በሚፈቅደው እንዲወሰን።
  የቦርዱ አባላት ተጠሪነታቸው ለመረጣቸው የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመን ስለሆነ ማናቸውንም የሚወስኑትንና የሚፈጽሙትን ጉዳይ ሁሉ በየስድስት ወሩ ለምዕመኑ በግልጽ እንዲያቀርቡ። ከምዕመናን የሚቀርቡላቸውን ጥያቄዎች፣ አዳዲስ ሃሳቦችን፣ ጥቆማዎችንና ማረሚያዎችን እንዲያስተናግዱ ይደረግ።
  ይህ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንጂ የቀበሌና የፖለቲካ ኮሚቴ ስላልሆነ ከምዕመናን ጋር መነታረክ፣ መሳደብ፤ መዝለፍ፤ ማበሳጨት እልክ መግባት እዚህ ቅዱስ ቦታ ውስጥ ፈጽሞ አላስፈላጊ መሆናቸው እያንዳንዱ የቦርድ አባል ሊገነዘበው ይገባል። አዲስ የሚመረጠው አመራርም ሆነ ሁሉም ምዕመናን በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የታነጹና ትሕትናና መንፈሳዊነትን የተላበሱ እንዲሆኑ በየጊዜው ኦርቶዶክሳዊ ትምህርትና ምክር እንዲሰጣቸው እናሳስባለን።
  3) በቤተ ክርስቲያኗ ዓውደ ምሕረት ስለሚሰጠው ትምህርት ሁኔታ፤
  በአውደ ምሕረቱ የሚሰጠው ትምህርት ኦርቶዶክሲያዊ ይዘትና መንፈሳዊነት አለው ወይ?
  ይህ ብዙ አባላትን ለረጅም ጊዜ ሲያነጋግርና ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ነው። አንድ ምዕመን ጊዜውን ሰውቶ፤ ብርዱን ተቋቁሞ ረጅም መንገድ ተጉዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣው ለምንድነው?
  በመጀመሪያ አንድ ሰው አውደ ምሕረቱ ላይ ወጥቶ ላስተምር ከማለቱ በፊት የሃይማኖት ትምህርት ብቃት፤ የስብከት ችሎታና መንፈሳዊነት እንዲኖረው የግድ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥና ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያለው ሕይወቱ ተመሳሳይና ተናግሮ ሌሎችን በሃይማኖት ለማነጽ የሚችል መንፈሳዊ ሰው መሆን ይገባዋል።
  እርግጥ ነው በመጀመሪያዎቹ አመታት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በሃይማኖት ትምህርት የዳበረ ሰው ስላልነበረ ማንኛውም ምዕመን እየተነሳና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለየ ስሜት ሰጥቶኛል የሚለውን ጥቅስ አውጥቶ ለምዕመናን ሲያካፍል፣ ምሥክርነትን ሲስጥ ቆይቷል። ይህ አሠራር ግን በቤተ ክርስቲያኗ አውደ ምሕረት ላይ ሳይሆን በሰንበት ትምህርት ቤት ጉባዔ ላይ ነበር። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁንና ባሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ ራሷ ያስተማረቻቸውና ያሰለጠነቻቸው በስልጣነ ዲቁናና፤ በስልጣነ ክህነት ያሉ ታላላቅ ደቀ መዛሙርትና ሊቃውንት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዕንቁና የሊቃውንት ቁንጮ ነው ተብሎ የተመሰከረለት መርጌታ ጭምር ስላሏት የሃይማኖቱ ትምህርትና ስብከት በእነሱ ይሰጥ።
  በኛ ቤተ ክርስቲያን ነገሮችን መጀመር እንጂ መፈጸም አልተለመደም እንጂ፣ ባንድ ወቅት ላይ ከመደበኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተጨማሪ፣ ላጭር ጊዜም ቢሆን፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜና የግዕዝ ትምህርትም ሳይቀር መሰጠት ተጀምሮ ነበር። ምዕመኑም ትምህርቱን ለመከታተል በከፍተኛ ጉጉትና መንፈስ በመነሳሳት ተዘጋጅቶ ነበር። ታዲያ ይህ አገልግሎት ለምን ተቋረጠ? ለምንስ አይቀጥልም?
  አውደ ምሕረቱ ስለ ምግብ መጠጥና ሰለሌላም ከሃይማኖት ትምህርት ውጭ ስለሆነው ነገር የመነጋገሪያ ጉባዔ አይደለም። ምዕመኑ በትዕግሥትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና የተቀመጠው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሲሰበክ ለማዳመጥ፣ ለመጸለይ፣ ለመዘመርና መንፈሳዊ ሕይወቱን ለመገንባት ነው። አንዳንድ ሰባኪዎችጭራሽ በማያውቁት ባልዋሉበት ባልተማሩትና ሙያቸው ባልሆነ የተለያየ የሥራ ዘርፍ ሁሉ ላይ ሳይቀር በድፍረት ገብተው ተራ አስተያየት ሲሰጡበትና ሲተቹበት ለመስማት የሚቀመጥ ምዕመን ያለ አይመስለንም። ስለዚህም ሰባክያን ወንጌሉንና ወንጌሉን ብቻ ያስተምሩ። በአውደ ምሕረቱ የሚነገርው ነገር በሌላ ጉባኤ ከሚነገረው ነገር በቋንቋውም በስሜቱም በትርጉሙም የተለየና ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ መሆን አለበት።
  የቤተ ክርስቲያን ፍቅር በውስጣቸው የሚቃጠለውን ምዕመናን የሚያሳዝንና ግራ የሚያጋባ ንግግር ሁሉ ከአውደ ምሕረቱ እንዲቀር ይደረግ። በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ስህተት እንዲታረምና ካሁን በኋላ ይህ አሠራር እንደማይቀጥል ለምዕመናኑ ግልጽ በሆነ መንገድ ይነገር። የምዕመናኑ ልብ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ ይደረግ።
  4) በዓውደ ምሕረቱ ስለሚሰጠው ትምህርት ይዘት፤
  የትምህርት አሰጣጡ ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት እንዳሰሰብነው ሁሉ፣ ይዞታውም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዶግማና ዕምነት ላይ የተመሰረተ ወንጌላዊ ትምህርት እንዲሆንና የማንንም ሃይማኖት የማይነካ፤ የማያንቋሽሽ፤ የምዕመናንን ስነ ልቦናና ስብእና የማይነካ፤ ሰላምንና ፍቅርን የሚያስተጋባ፣ የእግዚአብሔርን ቸርነት አባትነትና መሃሪነትን የሚያሳይ ብቻ እንዲሆን እናሳስባለን።
  5) ከቤተ ክርስትያን ስለቀሩት የድሮ አባላት ጉዳይ፤
  የቤተ ክርስቲያኒቱ ነባር አባላትና አገልጋዮች ምክንያቱ ባልታወቀ ነገር በየጊዜው ሲቀሩ ለምን ቀሩ፤ ቅር የተሰኙበት ነገር ካለ እናናግራቸውና መፍትሄ ይፈለግ እንላለን። ባሁኑ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን የራቁት ምዕመናን ለጥላቻና ተራ ለሆነ ሃሜታም እንዲጋለጡ ሆነዋል። ይህ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን የማይጠበቅ ተግባር ስለሆነ ባስቸኳይ መታረም አለበት። ነገራችን ሁሉ እውነትንና እውነትን ብቻ የተመረኮዘ ይሁን።
  በሌላ በኩልም የዊኒፔግ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ታውቃለች፣ አድጋለች፣ ተመንድጋለች ይኸውና እድገቷንም በኢንተርተርኔት እያሰራጨች ነው እየተባለ ይነገረናል። ለዚህም ሲባል በቤተ ክርስቲያን የተነሱ ፎቶዎችና የቪድዮ ክሊፖች በኢንተርኔት ላይ ሲወጡ ይታያሉ። ነገሩ የወንጌልን ትምህርት ለማስፋፋት የሚል ይዘት ያለው ይመስላል። ይህ ግን ሀሰት ነው። ይህ ድርጊት “ራስ ሳይጠና ጉተና” ወይም “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” የምባለውን የአበው ተረት ያስታውሰናል። የኢንተርኔቱ ዝና ይቆይልንና ቤተ ክርስቲያኒቱ የተበታተኑትን አባላቶቿን ትሰበስብ፣ ልጆቿን ታስተምር፣ ቤቷንም ታጠናክር። የራቁትንም ምዕመናን ምክንያታቸውን ትጠይቅ። ተመልሰው እንዲመጡም አስፈላጊው ሁሉ ታመቻችላቸው። በዚህ ውኒፕግ ከተማ በተራራ ላይ እንዳለ ፋኖስ ታብራ። የፍቅር የሰላምና የአንድነት ማእከል ትሁን።
  6) ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት፤
  የሰንበት ትምህርት ቤት ተቋቁሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለምዕመናን እንዲሰጥ ይደረግ። የማስተማር ጥሪና ተስጥዎ አለኝ የሚል ምዕመን ሁሉ አውደ ምሕረቱን ለካህናቱ ይልቀቅላቸውና በዕውቀቱና በችሎታው ለማገልገል በዚህ የሰንበት ትምህርት ቤት ጉባዔ ቦታ ይሰጠው።
  7) ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ገቢና ወጭ፤
  ባሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ ምን ያህል ገቢ ምን ያህልስ ወጭ እንዳላት ለምዕመናኑ በግልጽ እየተነገረ አይደለም፡፡
  የሚያሳዝነው ነገር ግን ይህ የቤተ ክርስቲያኗ የገቢና ወጭ ጉዳይ ሚስጢር ሆኖ የተያዘው ዝቅተኛ ሥራ ሠርተው በሚያገኙት ገቢ ቤተ ክርስቲያኗን ለሚያስተዳደሩት ምዕመናን እንጂ የካናዳ መንግስት በኢንተርኔት ስለሚያሰራጨው ማንም ሰው በግልጽ ሊያገኘው የሚችል ሰነድ ነው። ታዲያ ለቤተ ክርስቲያኗ አባላት ለራሳቸው ለምን የገዛ ቤተ ክርስቲያናቸው ጉዳይ ምስጢር እንዲሆንባቸው ተፈለገ? ለምንስ በግልጽ አይነገራቸውም?
  ሌላው ጉዳይ ምዕመናኑ የቤተ ክርስቲያኗ ገቢና ወጭ ኦዲት እንዲደረግ ውጤቱም በግልጽ እንዲነገራቸው በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም ጉዳዩ መልስ ሳያገኝና የቤተ ክርስቲያኗ የገንዘብ ጉዳይ እንደተሸፈነ ሆኖ አዲስ ለሚገነባው ሕንጻ ማሠሪያ የሚያዋጣው ሰው ስሙ እየተጠራና ስንት እንደሰጠ እየተነገረ ይጨበጨብለታል።
  ለማዋጣት የፈለገ ለቤተ ክርስቲያኑ ያዋጣ። ጭብጨባ አያስፈልገውም። የሚያዋጣውም እንዲንጨበጨብለት ብሎ አይደለም። ስለሆነም ይህ የየዋህነት አሠራር ከአውደ ምሕረቱ ቢወገድለት ምዕመኑ ደስ የሚለው ይመስለናል።
  ባሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በዛ ያሉ ዲያቆናትና ካህናት አሏት። ሆኖም ከካህናቱ እነማን በደመወዝ እነማንስ በነጻ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ በግልጽ ይነገር። በነጻ የሚያገለግሉትም ስላገልግሎታቸው የሚገባቸውን ምስጋና ይቅረብላቸው፣ ይጸለይላቸው። ደመወዝ የሚከፈላቸው ደግሞ ተጨማሪ አገልግሎት ይመደብላቸው።
  ለቤተ ክርስቲያኗ አንድነትና ህልውና ሲባልም ይህ ግልጽ ሲወጣ በከተማው የሚወራው አላስፈላጊ ወሬ፣ ይህንን በተመለከተ የሚሰራጨው ውንጀላና ስም ማጥፋት ሁሉ ይቆማል። ቤተ ክርስቲያኗም ሰላም ታገኛለች ብለን እናምናለን።
  8) ስለ ገንዘብ አሰባሰብ፤
  ባሁኑ ጊዜ ምዕመኑ በሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ያስቀምጣል። ከተለመደው የገንዘብ አሰባሰብ ዘዴ በተጨማሪ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ኤንቬሎፕ ቢዘጋጅና ምዕመኑ በተዘጋጀው ኤንቬሎፕ ስጦታውን አስቀምጦ ስሙን ጽፎ ቢሰጥ ለታክስ ማስቀነሻ ሊሆን ከመቻሉም በላይ ለቤተ ክርስቲያኗም ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ይሆናል ብለን እናምለን።
  9) ካህናት ስለሚሰጡት አገልግሎት፤
  ቤተ ክርስቲያኗ ባሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው በዛ ያለ ካህናት አሏት። ሆኖም ምዕመኑ በቂ አገልግሎት እያገኘ እንዳልሆነ ይነገራል።
  ካህናቱ በሳምንት አንድ ቀን ዕሁድ ከምዕመናኑ ጋር ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ይታያሉ። የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት እንዳበቃም በመጡበት አኳኋን እንደገና ከምዕመኑ ጋር ተቻኩለው ወጥተው ሲሄዱ ይስተዋላሉ። ስለዚህም ከካህናቱ የምክር፣ የንስሀ፣ የትምሀርትና ሌላም አገልግሎት የሚፈልግ ምዕመን አገልግሎት የሚሰጠው አጥቶ ሲቸገር ይታያል። ይህ አሠራር ትክክል አይመስለንምና ይስተካከል።
  የቤተ ክርስቲያኗ ሕንጻ በሳምንት ስድስት ቀናት ተቆልፎበት ይከርማል። በሳምንት ውስጥ ላንድ ቀን ብቻ (እሁድ) ለዚያምው ለተወሰነ ሰዓታት ይከፈታል።
  ከኛ ቤተ ክርስቲያን በስተቀር ባለንበት አገር እንኳንና ከሁለት መቶ ምዕመናን በላይ የሚገኙበት ደብር ቀርቶ ከሃያ ያልበለጡ ምዕመናንን ያቀፈ ቤተ ዕምነት ሁሉ ቢሮ ከፍቶ ሳምቱን ሙሉ በሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ላይ ምዕመናንን ሲያስተናግድና ሲያገለግል ይታያል። በዚህ አኳያ የኛ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ከየት የመነጨ እንደሆነ አይታወቅም።
  ሆኖም ይህ መለወጥ ያለበት አሠራር ነው። ደሞዝ የሚከፈላቸው ካህናት፣ ቢያንስ ቢያንስ በሳምንት ሶስት ቀናት የሥራ ሰዓት ተለይቶላቸው የቤተ ክርስቲያኗን ቢሮ ከፍተው ምዕመኑ የሚፈልገውን አገልግሎት ለማስተናገድና ለማስተማር ዝግጁ ሆነው መገኘት ይገባቸዋል።
  10) ስለ ካህናት ስነ ምግባር፤
  በቤተ ክርስቲያናችን ደንብ መሠረት ካህን ጥፋት አድርጓል ሲባል ጉዳዩ ለጳጳስ ተነግሮ ከስህተቱ እንዲታረም ይደረጋል። የኛ ቤተ ክርስቲያን ተጠሪነቷ ለየትኛው ጳጳስ እንደሆነ ለምዕመናን በግልጽ ስላልተነገረ በካህናቱ አካባቢ አንዳንድ ያላስፈላጊ ነገሮች ሲከሰቱና የሐሜት ውንጀላዎች ሲናፈሱ ለማን መነገር እንዳለበት ግልጽ አይደለም። የሚከሰቱትን ጉዳዮች ተመልክቶ አስፈላጊውን ውሳኔ የሚሰጥባቸው የበላይ ጳጳስ ባለመኖሩ ወደ ፖሊስና ወዳገሪቱ ሕግ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ሥጋትም አለን። ወደ ፖሊስና ሕግ ከተደረሰም ውጤቱ የቤተ ክርስቲያናችንን ባጀት የሚያቃውስ ከመሆኑም በላይ ክብሯን የሚያሳንስ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም የሚከስተውን ውንጀላ በግልጽ መርምሮ የሚወስን ጳጳስ እንዲኖረን ያስፈልጋል። ካህናት ሥጋ ለባሽ ሰዎች እንጂ መላእክት አይደሉም። ሰው ደግሞ ፍጹም ስላልሆነ፣ ካህናቱ ሲሳሳቱ ተሳስተሃልና ከስህተትህ ተመለስ፣ ንሥሃ ግባ የሚል የበላይ ጳጳስ እንዲኖረን ያስፈልጋል።
  ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ባሁኑ ወቅት ያሜሪካና ያገር ቤት ሲኖዶስ ተብላ በሁለት ጎራ ብትለይም የዊኒፔግ ቤተ ክርስትያን የበላይ ሳይኖራት መቀጠል የለባትም የሚል ዕምነት አለን። የእስካሁኑ እግዚአብሔር በቸርነቱ ከችግርና ከአደጋ ሰውሮናል። ለወደፊቱ ግን ችግሩ ከካህናቱ አልፎ ለምዕመናንም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚደርስ እንዳይሆን ይህ ጉዳይ ከወዲሁ በግልጽ ታስቦበት መፍትሄ ሊደረግበት ይገባል።
  ከዚህም በተጨማሪ፣ አንድ ካህን ከምዕመናን የሰማውን ምስጢር ማውጣትና ሃሜታ ውስጥ ፈጽሞ መግባት የለበትም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን በተለያዩ ቦታዎች እንደተገለጸው፣ እንኳንና የብዙ ምዕመናን ነፍስ ሃላፊነት የተጣለበት በክህነት የሚኖር ሰው ቀርቶ ማንም ተራ ምዕመንም ቢሆን ሀሜታ፣ ወሬና አሉባልታን ካንዱ ወደ አንዱ ከማመላለስ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ተገልጿል። በኦርቶዶክሳዊ ባህላችንም ከካህን ጋር የተወራ ምስጢር ከቁርባን ተለይቶ ስለማይታይ ምስጢርነቱም የቁርባን ያህል ከባድ ነው። በሌላ በኩልም፣ ሀሜትና ወሬ ሰውን ያጣላል፣ ትዳርን ያፈርሳል፣ ጓደኛንና ቤተ ሰብን ያለያያል። ጦሱ ያገሪቱን ሕግ ለመጣስና ወንጀል ውስጥ ለመግባትም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ስለዚህም አንድ ካህን ምስጢር መጠበቅ ይገባዋል። ያለበለዚያ ምዕመናን በካህኑ ዕምነት ስለማይኖራቸው ምክርም ሆነ ንስሃ ፍለጋ ወደ እርሱ አይደርሱም። ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አይሆንም። ይህም ለካህናቶቻችን የምናካፍለው ወንድማዊ ምክር ነው።
  11) ስለ ሕጻናት ትምህርት፤
  ቤተ ክርስቲያን በጣም ጠንክራ መሥራት ያለባት ሕጻናትን በማስተርማርና በማነጽ ላይ ነው። የኛ ቤተ ክርስቲያን ግን በዚህ ዙሪያ ጭራሽ ትኩረት አልሰጠችበትም። ይልቁንም ሕጻናቱ ምድር ቤት ተሰብሰበው ሥነ ሥርዓት በሌለው መንገድ ሲጯጯሁ ዞር ብሎ የተመለከታቸው አንድም ሰው የለም። ሕጻናቶቻችን ቤተ ክርስቲያን ሂደን ይህን ተምረን ተመለስን የሚይሉበት ሁኔታ የለም። ታዲያ እንዴት ሆነው ነው እነዚህ ህጻናት የዚች ቤተ ክርስቲያን የነገ ተረካቢዎች የሚሆኑት? ሌሎችን በዕምነታቸው ለመዝለፍ ከመቸኮል በፊት የኛ ቤተ ክርስቲያን ምን እያደረገች ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።
  ስለዚህም በሌሎች ቤተ ክርስቲያናት እንደሚደረገው ሁሉ በሥነ ሥርዓት ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖታቸውን ሊማሩ የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻችላቸው እናሳስባለን።
  12) ስለ መኪና ማቆሚያ፤
  ቤተ ክርስቲያኗ ለምዕመናኗ ሥርዓት አታስተምርም ወይ የሚያሰኛት ሌላ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኒቱ መኪና ማቆሚያ የሚታየው ሕግ የለሽ የመኪና አቋቋም ነው። በከተማው ብዙ ቤተ እምነቶች አሉ። ባንዳቸውም ውስጥ የኛን የመሰለ ሕገ ወጥ የመኪና አቋቋም አይታይም።
  ላዲስ መጭዎች፣ ለእንግዶችና ባካባቢው ለሚኖረው ሕብረተሰብ በሚያስገርም ሁኔታ ከስነ ሥርዓት ውጭ መኪናዎች ይቆማሉ። ለዚህ ጉድለት ተጠያቂው ማንው ቢባል ያው አስተዳደሩ ነው። ይህን የሚያስፈጽምና የሚከታተል ኮሚቴ መመደብ ሲገባው ይህ አልተደረገም። ስለዚህም ይህ ሥነ ሥርዓት የለሽ አሠራር እንዲወገድ ይደረግ።
  13) ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ጥገና፤
  የቤተ ክርስቲያኗ ሕንጻ እየፈራረሰ ነው። አስፈላጊው ጥገና ሊደረግለት ሲገባ ማንም ዞር ብሎ እያየው አይደለም። አሁንም ይህ ጉዳይ አስተዳደሩን ይመለከታል። ብዙ በዚህ ባጭር ዘገባ የማናሰፍራቸው ጉዳዮች አሉ።
  በመጨረሻ ሁሉም ነገር ስለ እኛ ሳይሆን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ታላቅነትና ክብር ስለሆነ በዚህ ጥቅስ እናጠቃልላለን፤
  ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡ 16
  “የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል”
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  ዶር ብርሃኑ ባልቻ……………………………………ሊቀ መንበር ____________________________________
  ሊቃ ትጉአን ያረድ አስቻለው……………………ጸሓፊ ___________________________________
  ለማ መኮንን…………………………………………….. አባል __________________________________
  አቻምየለሽ አስፋው……………………………….. .አባል ____________________________________
  መንግስቱ አያለው………………………………… አባል _____________________________________

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: